
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በሩዝ ማሣ ውስጥ የዓሣ ጫጩት የማልማት ሥራ ተጀምሯል፡፡ በሥራውም በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየኾኑ መጥተዋል፡፡
ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የዓሣ ምርት የፎገራ ወረዳ የልማት ቀጣና ከሚታወቅባቸው የግብርና ሀብቶቹ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ሃብቶች በተለያዩ አማራጮች አልምቶ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በእንስሣትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፉም ትኩረት ተሠጥቶታል፡፡
የዓሣና ሩዝ ጥምር ግብርና ልማት ዓሣን በሠፊ ባሕር ብቻ ማምረት ተረት ያደረገ አዲስ የጥምር ግብርና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አርሶ አደሮችንም አመጋገባቸውን ከማሻሻሉ በላይ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ኾኖ እያገለገለ ነው፡፡
በወረታ ዙሪያ ወረዳ የቁሃር አቦ ቀበሌ አርሶደር ማሩ አለምነው ዓሣን በሩዝ ሰብል ሥር በማርባት ተጠቃሚ መኾን የጀመሩት በ2014/15 የምርት ዘመን ነው። በተደረገላቸው ሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በ2014/15 የምርት ዘመን በቤት ውስጥ ከተመገቡት በተጨማሪ 20 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመንም ዓሣዎችን ከሩዙ ማሣ ላይ መጨመራቸውንም ገልጸዋል፡፡ አርሶአደር ማሩ አሁን ላይ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የዓሣ መኖ አለመቅረቡን እና የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶአደር በየነ ሙሉ ዓሣና ሩዝን በጥምር በማልማት ገቢ ማግኘታቸውን ያነሳሉ፡፡
ዓሣን በቤታቸው መመገብ መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ከዓሣ ሽያጭ 6 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጣና ዙሪያ ይኑሩ እንጂ ዓሣ ተጠቃሚ ባለመኾናቸው ባለፈው ጊዜ መጸጸታቸውን ጠቁመዋል፡፡
አርሶአደር በየነ ያመረቱትን ዓሣ ለችግር እንዳይጋለጥ ለቀጣይ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ተይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዓሣ ቴክኖሎጂ ባለሙያና በተቀናጀ ሩዝና ዓሣ ግብርና ልማት አስተባባሪ አበበ ፈንታሁን የተቀናጀ ሩዝና ዓሣ ግብርና ልማት ፕሮጀክቱ በ2012/13 የምርት ዘመን በደቡብ ጎንደር ፎገራ ወረዳ በ2 ቀበሌዎች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በሥራው ላይ 50 የሚደርሱ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
ምርታማነቱ ከአርሶ አርሶ አደር አርሶ አደር የሚለያይ ቢኾንም ከ625 ካሬ ሜትር የሩዝ ሰብል ውስጥ በሚያለሙት የዓሣ ምርት ከ4 ሺህ እስከ 22 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውንም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
በ2015/16 የምርት ዘመንም ጥምር ግብርናውን በማስፋፋት ከፎገራ ወረዳ በተጨማሪ ወረታ ከተማ አሥተዳደር ዙሪያ ቀበሌዎች፣ ሊቦ እና ደራ ወረዳዎች ተሳታፊ እንዲኾኑ ተደርጓል፡፡ በመደበኛ ልማት ፕሮግራምም በ4 ወረዳዎች 41 አርሶአደሮች እንዲያለሙ መደረጉን አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በእያንዳንዱ ወረዳ ከ40 እስከ 50 አርሶ አደሮች እንዲሚሳተፉ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
“ከእርሻ እስከ ጉርሻ” በሚል መሪ ሀሳብ በማሠልጠን፣ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ፣ የዓሣ ጫጩቶችን፣ ቀለብና መረብ በማቅረብ፣ የዓሣ ምግብ አዘገጃጀትን ተግባራዊ ሥልጠና በመስጠት ለአርሶአደሮቹ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡
የሩዝ ሰብሉ ከተሰበሰበ በኋላም የሚተርፈው ዓሣ እስኪሸጥ ወይም ለምግብነት እስኪውል ድረስ የሚቆይበት የማኅበረሰብ ኩሬ ለማዘጋጀት የቦታ ርክክብ መደረጉንም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡
ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ምርታማነቱን ለማስፋትም የ5 ዓመት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ የደቡብ ጎንደር እና ሌሎች ዞኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተዘጋጅቶ ለግብርና ሚኒስቴር መቅረቡን አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡
የጥምር ግብርና ልማቱ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ በመኾኑ በልማቱ ለመሳተፍ በርካታ አርሶ አደሮች ጥያቄ በማቅረብ ላይ መኾናቸውን ከጽሕፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!