“ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሁለት ወራት ውስጥ 297 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል” የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት

57

ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተደረገ ያለው ሕዝባዊ ተሳትፉ በ2016 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኀይሉ አብርሃም እንዳሉት ባለፉት 12 ዓመታት ከ18 ቢሊዮን 350 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡

ከዚህ ውስጥ 15 ቢሊዮን 881 ሚሊዮን 551 ሺህ የሚኾነው በሀገር ውስጥ የተሰበሰበ ነው። 1 ቢሊዮን 419 ሚሊዮን 871 ሺህ ብር ደግሞ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ቦንድ ሽያጭ እና በስጦታ ተገኝቷል። ቀሪው ደግሞ በ8100 አጭር የመልእክት ቁጥር እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ አካውንት የተሰበሰበ ነው ተብሏል፡፡

በ2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ መጨረሻ ባሉት ወራት ከ1 ቢሊዮን 447 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ያነሱት ዳይሬክተሩ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ኀይሉ አራተኛ ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን ተከትሎ በተሠራው ሥራ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ብቻ ከ297 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትጵያውያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ነው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በገንዘብ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ ለሀገራቸው አምባሳደር ኾነው እያገለገሉ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቀሪ ሥራዎች ሙሉ በመሉ እንዲጠናቀቁ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የታየውን ውጤት ለመቀየር ከታች ጀምሮ የሚሰጠው ፈተና ይጠናከራል” የትምሕርት ምዘናና እና ፈተናዎች አገልግሎት
Next articleበሩዝና አሳ ጥምር ግብርና የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠሩ መኾኑን የደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡