
ባሕር ዳር: ጥቅምት 2/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የገጠመውን የውጤት ማሽቆልቆል ለመቅረፍ ከታች ጀምሮ የሚሰጠው ፈተና እንደሚጠናከር የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች አገልግሎት ገለጸ፡፡
በአገልግሎቱ የፈተና አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ወንደሰን ኢየሱስወርቅ ለውጤት መቀነስ አንዱ ምክንያት ተማሪዎች በታችኞቹ የትምህርት ደረጃዎች በተገቢው ፈተና እየወሰዱ አለመምጣታቸው ነው ብለዋል።
ይህም ተማሪዎች በየደረጃው ማወቅ ያለባቸውን እንዳያውቁ ማድረጉን ገልጸው፤ በስተመጨረሻ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ተማሪዎች በተገቢው ምዘና እንዲያልፉ ይደረጋል በማለት ገልጸው፤ ይህንንም ለመተግበር በ8ኛ ክፍል የሚሰጠውን ፈተና ከማጠናከር ባለፈ በየትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን ምዘና ለማጠናከር እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ፋና እንደዘገበው ከዚህ ባለፈ ግን ሁሉን አቀፍ የማሻሻል ሥራዎች እንደሚያስፈልግ የፈተናዎች ሥራ አስፈፃሚ ወንድወሰን ኢየሱስ ወርቅ ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!