
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መካሄዱን ቀጥሏል። የሊጉ 2ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር ዛሬ አርብ ሁለት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
9 ሰዓት ላይ ሀምበሪቾ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ። ምሽት 12 ሰዓት ደግሞ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን ይገናኛሉ።
ሀምበሪቾ በመጀመሪያው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲጫወት ያሳየውን የተከላካይ መሥመር ውስንነት አጠናክሮ ወደ ሜዳ መግባት ያስፈልጋል። ተጋጣሚውን ክለብ የአምናውን የሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመርታት በሥነ ልቦናም ዝግጁ መኾንን ይጠይቃል። በአንጻሩ የመጀመሪያውን የሊጉን ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን 4 ለ 1 በመርታት በድል የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድል የመጣ በመኾኑ ወቅታዊ አቋሙን የበለጠ በማጠንከር የጨዋታው ድምቀት ሊኾን ይችላል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ መድንን የሚገጥመው ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሲጫወት የታየበትን የተከላካይ መስመር መዘናጋት አርሞና የኢትዮጵያ መድንን ፈጣን አጥቂዎች ኳስ ማስጣል ከቻለ በዛሬው ጨዋታ ጣፋጭ ድል ይጎናጸፋል።
ፈሲል ከነማ በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ሦስት አቻ የተለያየ ሲኾን ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ባሕር ዳር ከተማን 3 ለ 2 መርታቱ ይታወሳል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!