በቀጣይ ጊዚያት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች ማመልከታቸውን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

23

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣይ ጊዚያት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች ማመልከታቸውን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት ገልጿል።

በኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጅ ትንበያ እና ቅደመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) በተለይ ለአሚኮ እንደገለጹት በበጋ ወቅት መደበኛ ዝናብ የሚያገኙት የሀገረቱ አካባቢዎች ማለትም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ ቦረና እና ጉጅን በመሳሰሉ ቦታዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

በአማራ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከዚህ በፊት የሚኖረው የአየር ኹኔታ ደረቅ እና ነፋሻማ ነበረ ያሉት ዶ/ር አሳምነው ዘንድሮ ግን ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች ያሳያሉ ነው ያሉት። በበጋ ወቅት መደበኛ ዝናብ የሚያገኙትን ጨምሮ በአማራ ክልል በቀጣይ ጊዚያት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለመኖሩ ዋና ምክንያት የፓስፊክ እና የሕንድ ውቅያኖሶች በከፍተኛ ኹኔታ መሞቃቸው ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በተለይም የሕንድ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ክፍል በከፋተኛ ኹኔታ መሞቁ በአማራ ክልል ለሚጠበቀው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ዋና ምክንያት መኾኑን አንስተዋል። የሚኖረው ዝናብም በግብርና ሥራ ላይ ሁለት መልክ ይኖረዋል ብለዋል። በበጋ ለሚዘሩ እና ገና ላልደረሱ ሰብሎች ምቹ ኹኔታን ሲፈጥር ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን ደግሞ እንዲበላሹ ያደርጋል ነው ያሉት።

አርሶ አደሮች በአግባቡ የደረሱ ሰብሎችን ቶሎ እንዲሰበስቡ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። ለበጋ የመስኖ ሥራ የተመቼ የአየር ኹኔታ እንደሚጠበቅ በመገንዘብም ሥራው በአግባቡ እንዲከናወን ብዙኅን መገናኛ ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት መረጃዎችን በማድረስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶክተር አሳምነው መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ጥሪ አቀረበ።
Next articleፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዛሬ ይገናኛሉ።