
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ጥሪ አቅርቧል።
በ2015/16 የምርት ዘመን በዞኑ 496 ሺህ 242 ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን ወደ 17 ነጥብ 17 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በሰላም እጦት ፣በዝናብ እጥረት ፣በግሪሳ ወፍ እና ቢጫ ዋግ ክስተት ምክንያት ወደ 65 ሺህ 512 ሄክታር መሬት ከምርት ውጪ ኾኗል፡፡
በዚህ ምክንያትም ከ901 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚታጣ ነው በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ተውልኝ ሽባባው የተናገሩት።
ከመምሪያው በተገኘው መረጃ መሰረት በስምንት ወረዳዎች ላይ 33 ሚሊዮን 300 ሺህ የሚገመት የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳል፡፡
የቢጫ ዋግ ክስተቱም 29 ሺህ 817 ሄክታር መሬትን ያዳረሰ ሲኾን 24 ሺህ 312 ሄክታር የሚኾነውን ለመከላከል ጥረት ተደርጓል ተብሏል፡፡
በአንዳንድ ወረዳዎች ያጋጠመው የዝናብ እጥረትም በምርታማነት ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል ነው የተባለው።
ተግዳሮቱ ከአርሶ አደሮች አልፎ የከተማ ነዋሪዎችን ለችግር ስለሚያጋልጥ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃዎችን መፈለግ እንደሚገባም ነው አቶ ተውልኝ ያነሱት።
በግብርናው ላይ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን የተጀማመሩ ሥራዎች እንዳሉም መምሪያው አስታውቋል።
በአንድ ተቋም ጥረት ስኬት ስለማይገኝ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ለዘርፉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በዚህ ጊዜ በአንዳንድ የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ ተጀምሯል፡፡
አቶ ተውልኝ እንዳሉት ተጨማሪ ጉዳት ላለማስተናገድ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በወቅታዊ ችግር ምክንያት ከብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጄንሲ የአየር ትንበያ መረጃን መደበኛ በኾነ መልኩ ማግኘት አልተቻለም፡፡
በመኾኑም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብን ጨምሮ ተገማች ያልኾኑ ችግሮች እንዳያጋጥሙ አርሶ አደሮች ያለምንም መዘናጋት ምርትን በአግባቡ እንዲሰበስቡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች በአካል በመገኘትም የድጋፍና ክትትል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!