
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የቀድሞ ተዋጊዎችን ከማኅበረሰቡ ጋር በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ፣ አቅም ግንባታ ፣ መረጃ ልውውጥ ፣ ምርምርና ዕውቀት ስርጸት፣ ሃብት ማሰባሰብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ነው የተስማሙት። ስምምነቱን የተፈራረሙት የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና የኢትዮጵያ ሲሺል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካይ ወይዘሮ ሃና ወልደገብርኤል ናቸው።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2022 በቅርቡ የተመሰረተ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በተደራጀ መልክ ሲንቀሳቀስ በነበረ ኃይል ውስጥ ነበሩትን የቀድሞ ተዋጊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በዘላቂነት እንዲዋሃዱ እና ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ የሚገባቸውን አበርክቶ እንዲወጡ ለማድረግ የሚረዱ ሥራዎችን ለማስተባበር ኀላፊነት ተሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በአንቀጽ 85 መሰረት የተቋቋመ ገለልተኛ ተቋም ነው። ምክር ቤቱ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኙትን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ በመወከል እንዲንቀሳቀስ በአዋጁ ኀላፊነት ተሰጥቶታል። በአሁኑ ወቅትም ከ4 ሺህ 700 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል ናቸው።
ኮሚሽኑ እና ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ተከታታይ ውይይቶች መሰረት የትብብር ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማ የተሃድሶ ሥራ ለማከናወን ነው ስምምነት ላይ የደረሱት። ይህ ስምምነት እና የጋራ ሥራ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የቀድሞ ተዋጊዎችን ለማቋቋም እና የታጠቁ አባላትን ጭምር ወደተረጋጋ ኑሮ በመመለስ ሂደት ውስጥ መሳተፋቸው ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በመግባቢያ ስምምነት ፊርማው ላይ ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!