
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስቲም ኢንኩቤሽን ማዕከል በተከታታይ ዓመታት ያስፈተናቸውን ተማሪዎች ሁሉንም አሳልፏል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል ቢገጥምም በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስቲም ኢንኩቬሽን ማዕከል ግን በተከታታይ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ ቀጥሏል፡፡
ለተከታታይ ዓመታት የተመዘገበው መልካም ውጤት ደግሞ ዘንድሮ ለሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ መነሳሳት መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ኢንኩቤሽን ማዕከል የ12ኛ ክፍል ተማሪው ኤርሚያስ ምሥጋናው ወደ ማዕከሉ በመግባቱ ተጨማሪ ግብዓቶችን እና ሰፋፊ ዕውቀቶችን ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ በሌሎች ትምህርት ቤቶች የማላገኛቸው ዕውቀቶችን አግኝቻለሁ ነው ያለው፡፡
ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየተማሩ መኾናቸውንም አስታውቋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ሁሉንም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የማሳለፍ ታሪኩ ለእነርሱም መነሳሳትን እንደሚፈጥር ነው የተናገረው፡፡ በእኛ ዘመን የተሻለ ውጤት እንጂ ያን ታሪክ የማያስጠብቅ ውጤት አይመዘገብም ብሏል፡፡
በትምህርት ቤቱ በተከታታይ የተመዘገበው ውጤት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያበረታታናል ነው ያለው፡፡ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ለትምህርት እንደሚያውሉትም ተናግሯል፡፡ መምህራን ጥልቅ ዕውቀት እንዲኖራቸው እና ለፈተና ዝግጁ እንዲኾኑ እንደሚያደርጓቸውም ገልጿል፡፡ ሁሉም ተማሪዎች በተከታታይ ማለፋቸው መነሳሳት ፈጥሮልናል ፤ በእኛም ጊዜ የተሻሉ ተማሪዎች ያሉበት ነው ፤ የተሻለ ውጤትም እናመጣለን ብሎናል፡፡
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙም መልእክት አስተላልፏል፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ጊዜያቸውን ለፈተና ዝግጅት እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ የሰላም እጦት የሥነ ልቦና ጫና እያሳደረባቸው መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሰላም ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ሰላም በጠፋ ጊዜ ተፈታኝ ተማሪዎች ብቻ ሳይኾኑ ወላጆችም የሥነ ልቦና ጫና እንደሚደርስባቸው ነው የተናገረው፡፡
ሌላኛዋ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዮስቲና አበራ በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ ስቲም እንኩቤሽን ማዕከል ከሌሎች ትምህርት ቤት በተለየ ተግባር ተኮር ትምህርት እንደሚሰጥበት ገልጻለች፡፡ በዩኒቨርሲቲ መምህራን መማራቸው ራሳቸውን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ አድርገው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸውም ተናግራለች፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት በጣም ጥሩ በመኾኑ ትምህርት ላይ ብቻ እንድናተኩር አድርጎናል ነው ያለችው፡፡
የትኛውንም የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተናግራለች፡፡ የተመቻቸ የመማር ማስተማር ሂደት በመኖሩ ራሳችንን ፈልገን እንድናገኝ አድርጎናልም ብላለች፡፡ የሚማሩበት ክፍለ ጊዜ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች አንጻር የተሻለ መኾኑንም ገልጻለች፡፡ መምህራን የተሻለ ዕውቀት እንዲኖራቸው መንገድ እንደሚከፍቱላቸውም ተናግራለች፡፡ መምህራን በፈለግነው ሰዓት እንድንጠይቅ፣ የፈለግነውን ሥራ እንድንሠራ ያደርጉናልም ብላለች፡፡ ወላጆችም ጥሩ እገዛ እንደሚያደርጉላቸው ነው የተናገረችው፡፡
በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በተከታታይ ሁሉም ማለፋቸው በሌላው ተማሪ መነሳሳት ፈጥሯል ብላለች ዮስቲና፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ለትምህርት ቁርጠኞች መኾናቸውንም ተናግራለች፡፡ በክልሉ ያለው የሰላም ኹኔታ ተማሪዎችን እንደሚያጨናንቅ የተናገረችው ዮስቲና ተማሪዎች በተቻለ መጠን የሥነ ልቦና ጫና ከሚፈጥሩ ወሬዎች ራሳቸውን በማራቅ ለተሻለ ውጤት መዘጋጀት አለባቸው ብላለች፡፡ የተሻለ ውጤት እንዲፈጠር፣ ጥሩ ትውልድ እንዲወጣ ለሰላም ሁሉም መሥራት አለበት ብላለች፡፡ ሕጻናት መማር ይፈልጋሉ እንዲማሩ ደግሞ የሥነ ልቡና ጫና የሚያሳድሩ ድርጊቶችን ማቆም መልካም መኾኑን ነው የተናገረችው፡፡
ለተሻለ ውጤት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና አለመሰልቸት እንደሚያስፈልግም ገልጻለች፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!