ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው 17ኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን አውደ ርእይ እየተካሄደ ነው።

39

አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው 17ኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን አውደ ርእይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።

ቀደም ሲል በየዓመቱ የሚካሄደው ኢትዮ-ኮን ዓለም አቀፋ የኮንስትራክሽን አውደ ርእይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰላም እጦት ምክንያት ነው ተቋርጦ ነው የቆየው። የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ግርማ ሀብተማሪያም የዘንድሮው አውደ ርእይ ከዛሬ ጥቅምት 1 እስከ 4/2016 ዓ.ም እንደሚቆይም ተናግረዋል።

ኢንጅነር ግርማ ባለፋት ዓመታት የነበረው ሀገራዊ ኹኔታ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውና በግንባታ ሥራ ተቋራጮች ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽኖ የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል። የነበረው አለመረጋጋት በግንባታ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት። በመስኩ ላይ የተሰማሩ ዜጎችም የሥራ አጥነት ችግር ገጥሟቸው ነበር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

ለተከታታይ 4 ቀናት የሚቆየው ኢት-ኮን ዓለም አቀፍ አውደ ርእዩ የዘመኑ የቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓት የደረሰበትን ደረጃ ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ግብይትንም ለማሳለጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ የግንባታ ዘርፉ ዋና ዓላማ ሀገር መገንባት ነው ብለዋል። የዘርፉን ደረጃ ከፍ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና ሀገር የሚገነባበት የማድረግ ሥራዎች በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገቡ ናቸው ብለዋል።

80 በመቶ የሚኾኑ የግንባታ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ መንግሥት እየሠራ ነው ሲሉም ኢንጅነር ወንድሙ ተናግረዋል። የግንባታ ችግሮችን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ:- ራሄል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የለውም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleበኮትዲቯር አዘጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ይፋ ኾነ።