“ኢትዮጵያን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የለውም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

56

ባሕር ዳር: ጥቅምት 1/2016ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው በመኾኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ልዩ አማካሪዋ አሊስ ዋይሪሙ ያወጡት መግለጫ ኃላፊነት የጎደለውና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የማያሳይ ነው ብሏል።

የልዩ አማካሪዋ መግለጫ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጣውን የተሳሳተ ሪፖርት መሰረት ያደረገ መኾኑንም ጠቅሷል።

ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበና አስተማማማኝ ካልኾነ የመረጃ ምንጭ የተሰበሰበ መኾኑን የገለጸው መግለጫው ይህም የሪፖርቱን ትክክለኛነት እና ተዓማኒነት ውድቅ የሚያደርግ ነው ብሏል።

በመኾኑም የዘር ማጥፋት ወንጀልን የመከላከል ትልቅ ኀላፊነት የተሰጣቸው ልዩ አማካሪዋ በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ያልተረጋገጠ ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨታቸው ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት መግለጫው አመላክቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የክትትል፣ አስከባሪና አረጋጋጭ ኮሚቴም ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ እንዲኾን ቁርጠኛ መኾኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ፍትሕና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ተገልጾል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ውይይቶችን በማድረግ ቁርሾዎችን በመሻር የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑም በመግለጫው ተነስቷል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሰላም ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዲኾን እና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም ድጋፉን ያጠናክራል ብላ እንደምትጠብቅ ተገልጿል።

በመኾኑም ልዩ አማካሪዋ የሰላም ሥምምነቱን በተመለከተ “ከዓመት በፊት የተደረሰው የሰላም ሥምምት ውጤት አላመጣም” በማለት ያስቀመጡት የተዘባ ግምገማ ትክክለኛ ያልኾነ በመኾኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው መግለጫው አመላክቷል።

የልዩ አማካሪዋ መግለጫ በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚቃረን በመኾኑ ሊያስተባብሉ ይገባል ብሏል መግለጫው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከዓለም አቀፉ የሰነደ መዋእለ ንዋይ እና ኢንቨስትመንት ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡
Next articleለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው 17ኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን አውደ ርእይ እየተካሄደ ነው።