
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከዓለም አቀፉ የሰነደ መዋእለ ንዋይ እና ኢንቨስትመንት ኢንስቲቲዩት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደ ሥነ ሥርአት ላይ ባለሥልጣኑ ለዩናይትድ ኪንግደም የካፒታል ገበያ ባለሀብቶች የመጀመሪያውን አማራጭና ያልተነካ የካፒታል ገበያ ሳቢ እድሎችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ በዩናይትድ ኪንግደም በይፋ መጀመሩን ያስታወቀው ባለሥልጣኑ የመግባቢያ ስምምነት ለባለስልጣኑ ተልእኮ ወሳኝ ምእራፍ እንደኾነ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ እንደተናገሩት በዓለም የፋይናንስ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ሲደረግ ዓለም አቀፍ ብቃት ፣ ዕውቀትና አቅምን መገንባት አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያ በሕግ ፣ በዕውቀትና በሥነ ምግባር የሚመራ ማድረግ ዋናው ተልእኳችን ነው ብለዋል ዶክተር ብሩክ። ፕሮፌሽናል የኾነ የካፒታል ገበያ ቁጥጥር ሥርዓትን እና የባለሙያዎችን የመቆጣጠር አቅም መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
ዶክተር ብሩክ ከካፒታል ገበያ የሚገኘውን የፋይናንስ አቅም በማሰባሰብ ለሀገር ኢኮኖሚና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ አዲስ ይሁን እንጂ ያልተነካ ፣ ለሀገር ውስጥም ኾነ ለውጪ ባለሃብቶች ከፍተኛ እድገትን ለማሰመዝገብ የሚያስችል አቅም ያለው የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመኾኑ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች በታሪካዊ እድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የሰነደ መዋእለ ንዋይ እና ኢንቨስትመንት ቻርተርድ ኢንስቲቲዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትሬስ ቪግሮ ስምምነቱ ሙያዊ ድጋፍን ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ለካፒታል ገበያ ባለሃብቶች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ያስችላል ፤ ከኢትዮጵያ የንግድና ፋይናንስ ሕግ ጋር የተጣጣመና በካፒታል ገበያ ባለሥልጣኑ የሚሰጡ የቁጥጥር ምዘናዎችን ለማደራጀት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ለፍቃድ ሰጪውና ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ ላይ ሙያዊ ድጋፍን ለመስጠት የሚያስችል መኾኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትሬስ ቪግሮ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒሰትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እንደተናገሩት መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ለሚያደርግለት የመጀመሪያውና ታሪካዊ በኾነው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ የፋይናንስ ኢንቨስትመንት እድል ተጠቃሚ እንድትኾኑ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ መልእክተኛና የፓርላማ አባል የኾኑት ሎረንስ ሮበትሰን በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ ከ 20 ዓመታት በላይ በሥራ ተመላልሻለሁ ለንግድና ኢንቨስትመንት ያለው ምቹ ኹኔታ በየጊዜው የተሻለ እየኾነ መጥቷል ብለዋል፡።
በሰው ኀይል ወጣትና ሰፊ የሥራ ፍላጎት ያለው ሕዝብና አበረታች የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ባለበት አሁን ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጪ ባለሀብት ክፍት በመደረጉ እጅግ የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ከዩናይትድ
ኪንግደም በፋይናስ ዘርፍና የካፒታል ገበያ ለሚሰማሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነት ለዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች አዲስ የካፒታል ገበያ እድልን የሚፈጥር በመሆኑ ሌሎች የካፒታል ገበያ ባለሀብቶች ወደዚህ አዲስ ገበያ እንዲገቡ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ መንግሥት ላለፉት ሦስት ዓመታት በወሰደው መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ሪፎርም በቴሌኮም ዘርፍ ግዙፍ የኾነውን ቮዳፎን ለመሳብ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ዩኒሊቨር ፣ ፒታርድስ ፣ ቫሳሪ ፣ ቴስኮ ፣ ዲያጆ ፣ ጂኤስኪ፣ ኬፊ ማእድን ፣ክላፍ ጂኦተርማልና ሌሎችም ግዙፍ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ ያፈሰሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ግዙፉ ዩኒሊቨር በማኑፋክቸሪነግ ዘርፍ ያለውን ኢንቨስትመንት ይበልጥ በማሳደግ ባለፈው ዓመት በኤምባሲያችን በተደረገው የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እንደሚያፈስ መግለጹን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተከፈተው የፋይናንስ ዘርፍ የዳበረ የካፒታል ገበያ ልምድ ያላቸው የእንግሊዝ ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍም እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በስምምነት ፊርማው ላይ የካፒታል ገበያ ባለሀብቶች ፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዳይሬክተሮች ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጪና ዓለም አቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት የሥራ ኀላፊዎች ፣ የፓርላማ አባላት ፣ ዳያስፖራውና እና ሌሎች እንግዶች እንደተገኙ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!