36

ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከሚደረገው ጊዜያዊ ድጋፍ በተጨማሪ ያለባቸውን የምግብ ክፍተት በዘላቂነት ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጅ ብዜት ዘር ምርምር ዳይሬክተር ሰማኝ አስረዴ (ዶ.ር) እንዳሉት በምሥራቅ አማራ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ፈጥነው ሊደርሱ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች እየቀረቡ ነው፡፡

የአማራ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ከሰቆጣ ዲክላሬሽን ጋር በመተባበር በአካባቢዎቹ አዳዲስ ዝርያዎች እንዲገቡ እያደረገ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

በተለይም “እንቁ ዳጉሳ” የተባለ ዝርያን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ያለውን የድርቅ ችግር ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም አካባቢው ባለፈው ዓመትም በድርቅ ተጎድቶ የተዘራው ማሽላ በደረቀበት ወቅት “እንቁ ዳጉሳ” የተባለውን ፈጥኖ የሚደርስ እና በሄክታር 15 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ዝርያ በማሰራጨት ችግሩን ለማቃለል አንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡

“እንቁ ዳጉሳ”ን በተለይም ቻይና እና ሕንድ በስፋት እንደሚጠቀሙበት ለአሚኮ የተናገሩት ዶክተር ሰማኝ ቆላ አንድ የሚባል ዝርያ ያለው በመኾኑ እና ሌሎች ዝርያዎችንም በማሻሻል የአካባቢውን ችግር ለመቅረፍ ስለሚያግዝ ችግሩ ያለባቸው አካባቢዎች በስፋት እንዲጠቀሙበት መክረዋል፡፡

በአካባቢው ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት የሚጠቅሙ ዝርያዎች እየተሞከሩ እንደኾነም ነግረውናል፡፡ እግረ መንገዱንም ለአካባቢ ማኅበረሰብ የሥነ ምግብ ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡

በቀጣይም ቀድመው የሚደርሱ የቦለቄ ዝርያዎች ስላሉ ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

ዶክተር ሰማኝ ዝርያው ቀድሞ ከመድረሱም ባሻገር በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር የተሻለ የሚባል በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

ሌላው ብርቱካናማ የስኳር ድንች ወደ አምስት የሚደርሱ ዝርያዎችን ለማየት ተሞክሮ “ኩልፎ” የተባለው ዝርያ የተሻለ መኾኑ በመረጋገጡ ከባሕር ዳር ወራሚት የማባዣ ጣቢያ ወደ አካቢዎቹ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ነው የሚገልጹት፡፡

በሰቆጣ የዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ላይ የሚባዙም “ሰቆጣ አንድ” የስንዴ ዝርያዎች ችግሩን ለመፍታት አማራጭ ኾነው ስለመቅረባቸው አብራርተዋል፡፡

በተለይም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በግብርና ምርምር የወጡ አዳዲስ ቀድመው የሚደርሱ ዝርያዎችን በስፋት ለመጠቀም እርብርብ ከተደረገ ችግሩን በአጭር ጊዜ መፍታት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ አጀንዳዎችን ላይ ተወያይቶ አጸደቀ።
Next articleየ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መካሄዱን ቀጥሏል።