
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 በጀት ዓመት ከ641 ሚሊዮን 465 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ 2 ሺህ 989 የተለያየ መጠንና ዋጋ ያላቸው የማምረቻ መሳሪያዎችን ለኢንተርፕራይዞች ማቅረቡን ነው አክሲወን ማኅበሩ ያስገነዘበው።
በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ለ1 ሺህ 478 ኢንተርፕራይዞች 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ከ3 ሺህ በላይ የተለያዩ መጠን ያላቸው ማሽኖችን ለማቅረብ ታቅዷል ተብሏል።
የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንዳለ ጌታሁን እንዳሉት አክሲዎን ማኅበሩ ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠር በሚችሉ እና የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት በሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ በአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ዋነኛ ትኩረት ቢሰጥም በኮንስትራክሽን፣ በእደ ጥበብ፣ በአገልግሎት እና ሜካናይዜሽን ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችም የመስሪያ ማሽን እያቀረበ ይገኛል።
አቅርቦት የሚደረግላቸው በዋናነት ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባስመዘገቡት ውጤት ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እና ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ነው።
ይሁን እንጅ በአመለካከትና አስተሳሰብ የተቀየሩ፣ የጠባቂነት መንፈስን ያስወገዱ፣ ሙያውና ክህሎቱ ያላቸው እንዲሁም ከተቋሙ የሚጠበቁ መስፈርቶችን ማሟላት ለሚችሉ ጀማሪ ኢንተርፕራይዞችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ገልጸዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በልብስ ስፌት፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በሌሎች የሥራ መሥኮች እንዲሰማሩ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል።
የካፒታል እቃ ፋይናንስ የሥራ እድል በመፍጠር እና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ፋይዳው የጎላ ቢኾንም ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ለማስቀጠል የገንዘብ አቅርቦት ችግር ዋነኛው ማነቆ መኾኑን ገልጸዋል።
የማሽን አቅርቦት፣ የዋጋ መጋነን እና የኀይል አቅርቦት የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች ሌሎች ፈተናዎች ናቸው ተብሏል። ችግሮቹ ከተፈቱ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ልማት ከማፋጠን ባለፈ ለበርካ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻል አንስተዋል።
አክሲዮን ማኅበሩ በ2016 በጀት ዓመት ለ1 ሺህ 478 ኢንተርፕራይዞች 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 3 ሺህ 275 የተለያዩ መጠን ያላቸው ማሽኖችን ለማቅረብ አቅዷል።
ድርጅቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ2007 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ 4 ሺህ 792 ኢንተር ፕራይዞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኾነዋል። ከ1 ቢሊየን 812 ሚሊዮን 475 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ 13 ሺህ 958 የተለያዩ ማሽኖችን ለኢንተርፕራይዞች በዱቤ ማቅረብ ተችሏል።
ኢንተርፕራይዞቹም ከራሳቸው ባለፈ እስከ አሁን ለ28 ሺህ 641 የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!