
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሚቀጥለው ዓመት በጀርመን ለሚዘጋጀው የዩሮ 2024 ዋንጫ ለማለፍ በርካታ ሀገራት ዛሬ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡
ዛሬ ሐሙስ ከሚደረጉ ማጣሪያ ግጥሚያዎች መካከል ስኮትላንድ ወደ ስፔን ተጉዛ በስታዲየም ኢስታዲዮ ዴ ላ ካርቱጃ የምታደርገው ጨዋታ በእጅጉ ተጠባቂ ኾኗል። የዕለቱን ጨዋታም በዋና ዳኛነት ጉዞቡዩኮ ይመሩታል ሲል ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በጨዋታውም ስኮትላንድ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ከቻለች በሚቀጥለው ዓመት በጀርመን በሚደረገው የዩሮ 2024 ውድድር ላይ የማለፊያ ትኬቷን ትቆርጣለች ተብሏል፡፡
ስኮትላንዳድ እስከ ዛሬ ያደረገችውን አምስቱን ጨዋታዎች በማሸነፍ በምድብ “ኤ” ውስጥ 15 ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን እየመራች ትገኛለች፡፡
ስፔን በበኩሏ በአሠልጣኝ ሉዊስ ዴ ላ ፉዌንቴ እየተመራች ስኮትላንድን ለመርታት ተዘጋጅታለች፡፡ ስኮትላንድ ያለመሸነፍ ጉዞዋን ለማስቀጠል ከባድ ፈተና ከስፔን በኩል ይገጥማታል።
ስፔን በ9 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትቀመጥም የምድቡ ሀገራት አምስት ጨዋታዎችን ሲያደርጉ እሷ ግን አራት ጨዋታዎችን ነው ያደረገችው፡፡
ዘጋቢ፡ ሙሉጌታ ሙጨ