
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም በበጀት ዓመቱ ከተያዘው እቅድ ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወዳጆቿን በማብዛት እና ጠላቶቿን በመቀነስ ስኬታማ ሥራ መሥራቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከያዘቻቸው እቅዶች ውስጥ በሩብ ዓመቱ ስኬታማ የኾነ የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ከተለያዩ ሀገራት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የነበሩትን ሥራዎች ውጤታማ በኾነ መንገድ በመከወን እቅዱን ማሳካት መቻሉን ነው የውጭ ጉደይ ሚኒስትሩ አምባሳደር መለስ ዓለም የተናገሩት።
በዚህም ከውጭ ግንኙነት ወይም ከዲፕሎማሲ አንፃር በሩብ ዓመቱ ስኬታማ እና ውጤታማ ሥራ የተሠራበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲን እንጠቀማለን ያሉት አምባሳደሩ እነዚህን ሁለት ዘውጎች ለማቅረብ ደግሞ አካታች የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እና መልከ ብዙ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን እንከተላለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም ተደማጭ ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብር ሀገር መኾኗን የምታረጋግጥ እና ለመኾን እየሠራች እንደምትገኝም ነው የውጭ ጉደይ ሚኒስትሩ አምባሳደር መለስ ዓለም የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!