
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሩዝ በስፋት ከሚመረትባቸው ዞኖች ውስጥ ደቡብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። ፎገራ ሩዝን በማምረት የኢትዮጵያን 58 በመቶ እና የአማራ ክልልን 70 በመቶ ምርት ይሸፍናል።
የክልሉ ግብርና ቢሮም ምርቱን በሰፊው ለማምረት በጣና ዙሪያና አካባቢው ባሉ ሩዝ አብቃይ ቦታዎች ሁሉ በመሥራት ላይ ነው።
በ2015/16 የምርት ዘመን ብቻ 50 ሺህ ሄክታር ማሳ በሩዝ ለመሸፈን ታቅዶ 49 ሺህ ሄክታር ማሳ ማልማቱን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ቀኛዝማች መስፍን ገልጸዋል።
ከነበረው 47 ኩንታል በሄክታር ምርታማነት ወደ 54 ኩንታል በሄክታር ለማሳደግም ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የተሻሻሉ አሠራሮች ጥቅም ላይ ውለዋል።
በምርት ዘመኑ 2 ሚሊዮን 700 ሺህ ኩንታል ሩዝ ለማምረት ታቅዶ መሠራቱን የተናገሩት አቶ ቀኛዝማች የግብዓት በተፈለገው መጠን አለመቅረብ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
ሩዝን በዘመናዊ የግብርና ልማት (ሜካናይዜሽን) ለማምረት ጅምር መኖሩንና ተጠናክሮ መስፋት እንደሚገባው፤ ለዚህም በዘርፉ ከተሰማሩ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና መንግሥታዊ ያልኾኑ የልማት ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራ ነው የተገለጸው።
ሩዝ በአማራ ክልል ትልቁ የገበያ ሰብል በመኾኑ እንደ ሀገርም ከውጪ የሚገባውን ለማስቀረት ታስቦ እየተሠራ መኾኑን በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሠብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡-
👉 ባለፉት ዓመታት ከ61 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለምቷል
👉 ለቀጣይም ለሩዝ ምቹ የኾኑ ቦታዎች ተለይተው 101 ሺህ ሄክታር ማሳ ለማልማት ታቅዷል
👉 እስካሁንም 83 ሺህ 650 ሄክታር በላይ የለማ ሲኾን ይህም የዕቅዱን ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል
ሩዝ አብቃይ ዞኖች አቅማቸውን አሟጠው ከመጠቀም አኳያ ውስንነት ስላለባቸው አዳዲስ ዞኖችን በተለይም ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ባሕር ዳር ከተማ እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወደ ማምረት ሥራው እንዲገቡ እየተደረገ መኾኑን አቶ አግደው ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ሩዝን በስፋት ለማምረት የማዳበሪያና የምርጥ ዘር እጥረት እንዲሁም ተዘዋውሮ ለመሥራትና ለመደገፍ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር መኖሩ በምርታማነቱ ላይ መሠናክል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ሩዝን በዘመናዊ ዘዴ በማልማት በብዛትም እና በጥራትም ለማምረት በተለይም የተሻሻለ የሩዝ መፈልፈያ ማሽንን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩን አቶ አግደው ገልጸዋል። ለዚህም በዘርፉ ከተሰማሩ መንግሥታዊ ያልኾኑ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር 9 ተጨማሪ የሩዝ መፈልፈያ ማሽኖች ግዥ ተፈጽሞ ሂደት ላይ መኾኑን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!