
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ኹኔታ ላይ ያወጣውን ሪፖርት እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡
የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘር ፍጅት ስጋት አለ በሚል ያወጣውን መግለጫ በመቃወም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫውም ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ ኹኔታ በተመለከተ ባወጣው ኀላፊነት የጎደለው እና መሠረተ ቢስ ክስ የኢትዮጵያን መንግሥት አሳዝኖታል ብሏል፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት ትክክለኛ የምርመራ ሂደትን ያልተከተለ እና ከትክክለኛ ምንጮች ያልተወሰደ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይገልፅ መኾኑን ጠቅሷል።
በሰሜኑ ክፍል የተከሰጠውን ጦርነት ለማስቆም ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሥምምነት መፈረሙን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ በዚህም በሰሜን የሀገራችን ክፍል የጥይት ድምፅ እንዳይሰማ ማድረግ መቻሉን አንስቷል፡፡
መንግሥት የፕሪቶሪያው ሥምምነት ተግባራዊ እንዲኾን ቁርጠኛ መኾኑን እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ተግባር እያከናወነ እንደኾነ ጠቅሷል።
በዚህም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ እና አሁንም ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት ወደ ሰላም ለመምጣት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል እየተሰራ እንደኾነም አንስቷል።
እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ይህ ባለበት ሁኔታ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከሽፏል በሚል የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው መኾኑን አስገንዝቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!