
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፈተናን አልፎ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ብርቅ በኾነበት፣ ብዙዎች ተፈትነው ጥቂቶች በሚያልፉበት፣ መምህራን ፍሬ ባጡበት፣ ተማሪዎችም የዓመታት ጉዟቸውን በስኬት በማይጨርሱበት፣ ወላጆች የድካማቸውን ዋጋ በማይከፈሉበት፣ ሀገር የልጆቿን ተስፋ በፈለገችው ልክ በማታገኝበት በዚህ ዘመን ብርቱ ልጆች ተገኝተዋል፣ ጀግና ልጆች ታይተዋል፡፡ ጀግንነት በየፈርጁ ነው፡፡ አንደኛው በጦር ሜዳ ምሽግ አፍርሶ ጠላትን ድል ያደርጋል፣ በደምና በአጥንቱ ሀገር ያጸናል፣ የአባቶቹን ታሪክ ይደግማል፣ የሀገርን ዳር ድንበር ይጠብቃል፡፡ ጠላቶቹንም እጅ ያስነሳል፡፡
ሌላኛው የዘመናትን ፈተና እየበጣጠሰ ይሻገራል፣ ብዙዎች ሲቀሩ ያለመናወጽ በትጋት ይገሰግሳል፣ ማዕበሉን በጥበብ እና በጽናት ያልፋል፣ ጨለማውን ይገፍፋል፣ ዘመኑን በብርሃን ይቀይራል፣ አንደኛው ደግሞ ለሀገሩ አዲስ ነገር ያሳያል፣ በቸገራት ጊዜ መፍትሔ ይዞ ይደርሳል፣ ጥልና ጥላቻን አጥፍቶ ፍቅርና ሰላምን ያነግሳል፣ የአዘኑትን እንባ ያብሳል፣ የተከዙትን ያበረታል፣ የተቅበዘበዙትን ያስጠልላል፣ የተጨነቁትን ያረጋጋል፣ በየፈርጁ ጀግኖች ሞልተዋል፡፡ በየትግል መስኩ ጀግኖች አይጠፉም፣ ድል አድርገው የሚያኮሩ አይነጥፉም፡፡
እልፍ ተማሪዎች ከዳገቱ መውጫ ላይ በቀሩበት፣ የመምህራን የዓመታት ድካም ፍሬ አልባ በኾነበት፣ የወላጆች ተስፋ ባልተሳካበት፣ የልጆች የዓመታት ጉዞ ባልሰመረበት በዚህ ዘመን ፈተና የፈተናቸው፣ ግን ደግሞ ያልጣላቸው ጀግና ልጆች ተገኝተዋል፡፡ በተማሪዎች ላይ የተቃጣውን ማዕበል በብርታት አሳልፈዋል፣ አንደኛውን ምዕራፍ በድል ተሻግረው ወደሌላኛው ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በአዲስ መልክ መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ታይተዋል፣ ለወትሮው በተማሪዎች ብዛት የሚጥለቀለቁት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ አጥተዋል፣ ከሚያልፉት ይልቅ የማያልፉት በርክተዋል፣ የልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የምሥራች ከሚቀያየሩት እናቶች ይልቅ የማይቀያየሩት በዝተዋል፣ የበዙ ትምህርት ቤቶች አንድም ፍሬ ሳያዩ ቀርተዋል፤ ለምን ቢሉ ተማሪዎቻቸው ፈተናዎችን አልተሻገሩምና፡፡
በዚያ ትምህርት ቤት ግን ብዙዎችን የፈተነው፣ በርካቶችን ከበር ወዲህ ያስቀረው ፈተና አቅም አልነበረውም፡፡ በርካቶችን ድል ቢያደርግም በዚያ ትምህርት ቤት ግን በተደጋጋሚ ድል ኾኗል፡፡
የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያ አዲስ በጀመረችው የ12ኛ ክፍል የፈተና ሥርዓት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት አንድም ተማሪ ሳያስቀር ሁሉንም ተማሪዎችን አሳልፏል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት በኢትዮጵያ የመጣው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በዚሁ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፡፡ ዘንድሮ በነበረው ፈተና እንደተለመደው ሁሉ ሁሉንም ተማሪዎች አሳልፏል፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት ፈተናን ማለፍ ብቻ ነው የሚታወቅበት፣ ጎበዝ ተማሪዎች በብርታት ይማሩበታል፣ በኩራትና በብርታትም ያልፉበታል፣ ሀገራቸው ትኮራባቸዋለች፣ ወላጆቻቸውም ይኮሩባቸዋል፣ ይመኩባቸዋል፡፡
ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያን ተማሪዎች ክፉኛ የመታው የውጤት ማሽቆልቆል ማዕበል በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መድረስ አልቻለም፡፡ ጠንካራ ተማሪዎች ገፍተው መልሰውታል፣ አሳፍረው ጥለውታልና፡፡
የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር በለጠ ኃይሌ ያስፈተናቸው ተማሪዎቻችንን ሁሉንም አሳልፈናል ነው ያሉን፣ በርካታ ተማሪዎችም ከስድስት መቶ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በዚያ ትምህርት ቤት ክፍለ ጊዜ አይዘጋም፣ መምህራን በብርታት ያስተምራሉ፣ ተማሪዎች በንቃት ይማራሉ፡፡ በዚያ ትምህርት ቤት ውስጥ በዋዛ የምታልፍ ሰዓት የለችም፡፡ ሁሉም በቁም ነገር ታልፋለች፣ ለቁም ነገር ትውላለች፣ ለቁም ነገር የዋለች ጊዜ ፍሬዋንም አሳምራለች፡፡
ርእሰ መመምህሩ በትምህርት ቤቱ የማይሸፈን የትምህርት ምዕራፍ የለም ነው ያሉን፡፡ ተማሪዎች ጊዜያቸውን የሚያውሉት ለመማር ማስተማሩ ሥራ ነው፡፡ መምህራን ተማሪዎችን ሊያግዝ የሚችልን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ፣ ለመማር ማስተማር ምቹ የኾነ ቴክኖሎጂንም ይጠቀማሉ፡፡ መምህራን የትም ቦታ ኾነው የተማሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱበትን አማራጭ ይጠቀማሉ፡፡ በጋራ በከፈቱት ቴሌግራም አማካኝነት ተማሪዎች እያነበቡ ጥያቄ በከበዳቸው ጊዜ ለመምህራን ጥያቄውን ያቀርባሉ፣ መምህራንም ባሉበት ኾነው ጥያቄያቸውን ይመልሳሉ፡፡ የተማሪዎች እና የመምህራን ብርታት እና ቅንጅት ውጤታቸውን ያማረ አድርጎታል ነው ያሉን፡፡
መምህራን እና ተማሪዎች በየቤታቸውም ኾነው ግንኙነታቸው አይቋረጥም፡፡ መምህራን ተማሪዎች በፈለጓቸው ጊዜ ሁሉ ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎችም መምህራን የሚሰጧቸውን ይቀበላሉ፣ አድርጉ የተባሉትን ሳያጓድሉ ያደርጋሉ ነው ያሉት ርእሰ መምህሩ፡፡ መምህራንም ትክክለኛ ነገር ነው የሚያስጨብጧቸው፣ የሚያስተምሯቸውን ይዘት በትክል ያውቁታልም ብለውናል፡፡
መምህራን ከመማሪያ መጻሕፍት ባሻገር ዋቢ መጻሕፍትን በመጠቀም አስፋፍተው በጥልቀት እንደሚያስተምሯቸውም ነግረውናል፡፡ ትምህርት ቤቱ ልክ እንደ ኮሌጅ ነው፡፡ የተሻሉ መምህራን ተመርጠው ነው የገቡት፣ ልጆቹም ጎበዞች ናቸው፣ የመማር ማስተማሩ መስተጋብር የሰመረ ነው ብለውናል፡፡ መምህራን ተማሪዎቻቸውን አብዝተው ይወዷቸዋል፣ ተማሪዎችም መምህራንን እንደ ወላጅ ይወዷቸዋል፣ በመካከላቸው ያለው መልካም ግንኙነት እና የወላጅና የልጅ ፍቅር ትምህርቱንና ውጤቱን ስኬታማ እንዲኾን አድርጎታል፡፡
ርእሰ መምህሩ እንደነገሩን ተማሪዎች መምህራንን አብዝተው ያከብሯቸዋል፣ አይገላምጧቸውም፣ እንደ አባት እና እንደ እናት ያዩዋቸዋል እንጂ፡፡ በትምህርት ቤቱ እጅግ በጣም ያማረ ግንኙነት ነው ያለው፡፡ መምህራንም ልጆቻቸውን ያከብሯቸዋል፣ ይወዷቸዋልም፡፡ መምህራን በኮሮና ቫይረስ እና በጦርነት ምክንያት የተቋረጠባቸውን ትምህርት ሳያጓድሉ ሸፍነውላቸዋል፣ በሚገባም አስተምረዋቸዋል ነው ያሉን፡፡
ለስኬታማ ውጤት የመማር ማስተማሩ ጤናማ መስተጋብር ወሳኝ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ መምህራን ደግሞ የሚያስተምሩትን ትምህርት በደንብ ሊያውቁት ይገባል፣ ተማሪዎችም የትምህርት ሰዓታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙት ይገባል ነው ያሉት፡፡ በሌላ አካባቢ ተማሪዎች ግማሽ ቀን ተምረው፣ ግማሽ ቀን ሌላ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ከፍተኛ ጫናም ይፈጠርባቸዋል፡፡ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግን የትምህርት ሰዓት አይጓደልም፣ በዚህም ምክንያት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል ብለውናል፡፡
የተማሪዎች ሥራ መማር ነው፣ የአስተማሪም ሥራ ማስተማር፣ ወላጅ ደግሞ ለልጆቻቸው ሰፊ ጊዜ መስጠት አለባቸው፣ ልጆች ከትምህርቱ ሥራ ውጭ በሌላ ሥራ ባይጠመዱና ባይጨናነቁ መልካም ነው፡፡ ከፍተኛ የኾነ የወላጅ ክትትል ያስፈልጋል፣ መምህራንም ክፍለ ጊዜያቸውን ሸፍነው ከመውጣት ባለፈ በትርፍ ጊዜያቸውም ተማሪዎችን ሊያግዟቸው ይገባል፣ በዚህም ጊዜ ተማሪዎች የበለጠ ይበረታሉ፣ መምህራንም ስለሚያስተምሩት ትምህርት እውቀታቸውን እያሰፉ ይሄዳሉ ነው ያሉት፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ሰፊ የንባብ ጊዜ ቢሰጧቸው እና ቢከታተሏቸው ያማረ ውጤት ይመዘገባልም ብለውናል፡፡ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በትኩረት እንደሚከታተልም ነግረውናል፡፡ በትምህርት ቤቱ ለመማር ማስተማሩ ይጠቅማሉ የተባሉ ሁሉ ይተገበራሉ፣ መምህራን አጋዥ ሞጂሎችን ያዘጋጁላቸዋል፣ ፈተናዎችን በተደጋጋሚ ይፈትኗቸዋል፣ ብርቱ እና ፈተናን የሚያልፉ እንዲኾኑ ያደርጓቸዋል፡፡
ሌሎች ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መምህራን ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም መክረዋል፡፡ ተማሪዎች የተሰጣቸውን ይይዛሉ፣ ትክክለኛውን ነገር ለማስተማር ደግሞ መምህራን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጥሩ ውጤት ከጠበቁ ጥሩ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፣ ያልሰጡትን ነገር ሊያገኙ አይቻላቸውምና ነው ያሉን፡፡ ክልሉ ብቁ ትውልድ፣ አኩሪ ውጤት ማግኘት ከፈለገ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ይገባዋልም ብለዋል፡፡
የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የተሟላ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ የተሟላ ድጋፍ ሳያገኝም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ የተሻለ ድጋፍ ካለው የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚቀጥልም ነግረውናል፡፡
ወላጆች በተማሪዎቹ ኮርተውባቸዋል፣ መምህራንም ተመክተውባቸዋል፣ ሀገርም ደስ ተሰኝታባቸዋለች፡፡ ተማሪዎችም በደስታ ተሞልተዋል፡፡ ባልተመቸ ጊዜ፣ ባልሰመረ ዘመን የሰመረ ውጤት አስመዝገበዋልና ምሥጋና ይድረሳቸው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!