
አዲስ አበባ: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከጥቅምት 1/2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ቁልፍ መሠረተ ልማት የሚያሥተዳድሩ ተቋማት ፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና 9 የምርምር ተቋማት በተገኙበት ይከብራል።
በሳይበር ደህንነት ወሩ የግል የሳይበርና ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ይኾናሉ ተብሏል።
የጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነት ወር በመባል የሚታወቅ ነው። በርካታ ሀገራትም የዜጎቻቸውን እና የተቋማቶቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውኑበታል።
በሀገራችንም የዜጎች እንዲሁም የተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቀሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እና በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
በመሆኑም በዚህ ወር የተቋማቱንና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና በማጎልበት ለሳይበር ደህንነት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡና ራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንዲችሉ የሚያግዙ የተለያዩ መርሐ ግብሮች የሚቀርቡበት መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ።
በዓሉ በዓለም ለ20ኛ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል ።
አሥተዳደሩ የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲሠራ ቆይቷልም ተብሏል።
ለሀገር ደህንነት የሚጠቅሙ፤ ለጸጥታ ተቋማት ደህንነት የሚኾኑ ሶፍትዌሮች እና ሃርድዌሮች በማልማት አስታጥቋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
አሥተዳደሩ በርካታ የሳይበር ጥቃቶችን ሲከላከል ቆይቷልም ነው ያሉት።
በ3ኛው የሳይበር ደህንነት ወር 50 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ እንደነበሩ እና ጥሩ የተቋማት ቅንጅት የታየበት እንደነበር ተናግረዋል ዋና ዳይሬክተሩ። ባለፈው ዓመት 96 በመቶ ወይንም 23 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማዳን የተቻለበት ዓመት እንደነበርም ገልጠዋል።
በአምስት ሁነቶች የሚከበረው 4ኛው በዓል ለሕዝቡ ትልቅ ስጦታ ኾኖ የተዘጋጀ “ስውሩ ውጊያ” የተሰኘ በእውነተኛ ክስተት ላይ የተመሠረተ ፊልም ጥቅምት 4/2016 ዓ.ም ይመረቃል።
ከጥቅምት 12/2016 ዓ.ም እስከ 15/2016 ዓ.ም የፓናል ውይይት ተካሂዶ ዓመቱን ሙሉ የተጠና የሳይበር ደህንነት ስጋት ምርምር ይፋ ይደረጋል ።
የንቃተ ህሊና ጥናት ውጤት ይፋ ይኾናልም ተብሏል። ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም በሚደረግ ውይይት ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።
የሳይበር ተደራሽነት ላይ ዓላማውን ያደረገ የሳይበር ፖሊሲ እና ስታንዳርድ በተመለከተ የበይነ መረብ ውይይት የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች በተገኙበት ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም ኹነት ይካሄዳል ነው የተባለው።
ከዩኒቨርሲቲዎች እና የጥናት እና ምርምር ተቋማት ጋር በጋራ የሳይበር ደህንነት ምርምር ጥናተ ውጤቶች ይፋ የሚደረጉበት ኹነት ይኖራልም ተብሏል።
ዋና ዳይሬክተሩ ሰለሞን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሂልተን እና ሌሎች ቦታዎች የሚደረጉ አውደ ርእዮችን እንዲጎበኙ እና የግልና የመንግስት የሳይበር ተቋማት ተገኝተው የገበያ ትስስርና የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!