
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኀይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት በቅርቡ ወደ ትግበራ ሊገባ መኾኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግሪን አፍሪካ ኢነርጂ ዓመታዊ ጉባኤና ‘የአፍሪካ የነዳጅ ሳምንት’ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ለጋሽ ድርጅቶች ተሳታፊ ኾነዋል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ በከፍተኛ የውይይት መድረኮች ላይ እየተሳተፉ ነው።
ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ እየገጠሟት ካሉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የኃይል ሽያጭ ዋጋ እንደሆነና በአፍሪካ ዝቅተኛ በሚባለው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ እየሸጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የግሉን ዘርፍ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የመንግሥትና የግል አጋርነት የትብብር ማዕቀፍ ድንጋጌዎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቀጣናዊ የኃይል ትስስር ላይ በትብብር እየሠራች እንደምትገኝና አሁን ላይ ለጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን ኃይል እየሸጠች መኾኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሙት የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነትም በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ሕልውናቸውንና ዘለቄታዊ አገልግሎታቸውን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አብራርተዋል።
ጉባኤው እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ላይም ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢዜአ እንደዘገበው ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
በስምምነቱ መሰረት በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ ሲሆን በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ታቅዷል።
የኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በሁለቱ ሀገራት በኩል በማከናወን በሦስት ዓመታት ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል ለደቡብ ሱዳን ተደራሽ የሚደረግም ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!