የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮቿን አቀረበች።

35

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢንቨስት አፍሪካ 2023” በሚል መሪ መልእክት ለንደን ላይ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ

ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከኢንቨስትመንት አማራጮች በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የካፒታል ገበያንና የሰነደ መዋእለ ነዋይ /Securities Market/ እድሎችን ለዩናይትድ ኪንግደም
እና ከተለያዩ ሀገሮች ለመጡ በፋይንናስ እና በባንክ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

10ኛ ዓመቱን በያዘውና ከመላው ዓለምና ከአፍሪካ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ያካተተው ኢንቨስት አፍሪካ 2023 ጉባኤ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው የመሩት የልኡክ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የሰነደ መዋእለ ነዋይ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት

ሆልዲንግ የሥራ ኀላፊዎች እና በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተገኝተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በጉባኤው ላይ በኮቪድ፣ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ድርቅን ተቋቁሞ የኢትየጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ 6 ነጥብ 1 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ከ126 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢኮኖሚ እድገቱ የግሉን ዘርፍ በማካተት ይበልጥ ለማደግ የሚችልበት እድል ተከፍቷል ብለዋል፡፡

በተለይም ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ትኩረቱ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገትን ለማስዝገብ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ማድረግ፣ የንግድና

ኢንቨስትመንት ማነቆዎችን በመፍታት የተሳለጠ ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ በግብርና፣

በማንፋክቸሪነግ፣ በቱሪዝም፣ በማእድን እና በአይሲቲ ዘርፍ ሰፊ እድሎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ያልነበሩ በአሁኑ ወቅት ግን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድርሻ 25 በመቶ ቀሪው ድርሻ ደግሞ በሀገር ውስጥና በውጪ ባለሃብቶች የሚሸፈንበት የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፍ፣ የሰነደ መዋእለ ነዋይ /Securities Market/ በቅርቡ ይፋ መደረጉን አስታውሰው እነዚህ እድሎች ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ ሰፊ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። ባለሃብቱ በዚህ ዘርፍ እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም የባንክ የሕግና የቁጥጥር ሥርአት ዝግጅቱ በመከናወኑ የባንክ ዘርፉን ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሊሊሴ ነሜ በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአንድ መስኮት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን፣ ባለሃብቱ
በማንፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቱሪዝም፣ በአይሲቲ፣ በማእድን ዘርፎቸ ላይ ቢሰማራ ትርፋማ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ሕጎችና መመሪያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ለማድረግ በየወቅቱ ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ካላት ምቹ የገበያ፣ የጉልበት እና የጥሬ እቃ አቅርቦት አንጻር ተመራጭ እንደሆነችም አስገንዝበዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። መላው ዓለምን ሊያገናኝ የሚችል የአየር መንገድ እና የካርጎ አገልግሎት ያላት፣ በቂና የሰለጠነ ወጣት የሰው ኀይልና ሸማች የሆነ ማኅበረሰብ ያላት መሆኗ ተመራጭነቷን ያጎላዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም፣ የሕግና የተቋማት ሪፎርሞችን በማካሄዷ የዩናይትድ ኪንግደም ታላላቅ ኩባኒያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት መቀጠላቸውን አስታውሰዋል። ኤምባሲው ለባለሃብቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሰረድተዋል፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት መስሪያ ቤት የሥራ ኀላፊዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በጉባኤው ላይ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ: በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ ሁሉንም ተማሪዎች ካሳለፉ አምስት ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው”ትምህርት ቢሮ
Next article“የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኀይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት ወደ ትግበራ ሊገባ ነው” የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር