
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክልሉ ቀደም ሲል በወራሪው ጦርነት አሁን ደግሞ በክልሉ ባለው የሰላም እጦት ምክንያት በበርካታ ችግሮች እየፈተነ ነው፡፡
ተማሪዎች የጥይት ድምጽ እየሰሙ ተምረዋል፤ የጥይት ድምጽ እየሰሙ ተፈትነዋል፡፡ አብዘኛዎቹ የክልሉ ተማሪዎች በጦርነት ምክንያት በወደሙ እና በተዘረፉ ትምህርት ቤቶች ለመማር ተገድደዋል፡፡ በፈተና ወቅት በተፈጠረ አለመረጋጋት ፈተናውን አቋርጠው የወጡ ተማሪዎች መኖራቸውም አይዘነጋም፡፡
ፈተናዎች ቢበዙም፣ የተገኘው ውጤት አጥጋቢ ባይሆንም፣ ሰላም ከተረጋገጠ፣ የተረጋጋ እና የተስተካከለ ትምህርት መሥጠት ከተቻለ ግን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ታይተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ከሰሞኑ ባወጣው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት 3 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ማለፋቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ አምስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ካሴ አባተ እንደ ሀገር አምስት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች አሳልፈዋል፤ ሦስቱ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
ደሴ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት፣ ሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአደሪ ትምህርት ቤት እና ባሕር ዳር ስቲም ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ዳይሬክተሩ ደሴ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት እና ባሕር ዳር ስቲም ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመትም ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን ማሳለፋቸውን ነው ያወሱት፡፡ ሁለቱ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮም ያለፈው ዓመት ውጤታቸውን ሳያጓድሉ ደግመውታል፡፡
በሐዲስ ዓለማየሁ አዳሪ ትምህርት ቤት እና በደሴ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት በእያንዳንዳቸው 16 ተማሪዎች 600 እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከሁለቱ ትምህርት ቤቶች በድምሩ 32 ተማሪዎች 600 እና ከዚያ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ የሐዲስ ዓለማየሁ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የተዘመገበው ውጤት ዝቅተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሁንም በርካታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከታች ጀምሮ መሥራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት የሚችሉ ልጆች አሉን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
በአማራ ክልል ጦርነት እና ግጭት በፈጠሩት ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ ሆነው የተፈተኑ ተማሪዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ተማሪዎች ጫናውን ተቋቁመው ያስመዘገቡት ውጤት ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ ወደ ፊት መሥራት ከተቻለ ተስፋ የታየበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በክልሉ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በትምህርት ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች እየተተገበሩ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ግብዓት እና ድጋፍ እየተጠናከረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፈተና በተሰጠባቸው ወቅቶች በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ትምህርት ሰጭ እና መነሻ መኾን የሚችል ነው ብለዋል፡፡ የተሻለ ዜጋ ለማፍራት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ያስፈጋልም ነው ያሉት፡፡
አቶ ካሴ ትምህርት ቢሮው አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነውም ብለዋል፡፡ በዘንድሮው የፈተና ሥርዓት ኩረጃ የቀነሰበት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!