
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በ2015 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎች ውስጥ 85 በመቶ 50 እና ከዚያ በላይ አስመዝግበዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አጸደወይን እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ካስፈተናቸው 72 ተማሪዎች 85 በመቶ የማለፊያ ነጥብ አስመዝግበዋል።
613 የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቱ ከፍተኛው ውጤት ሲኾን ዘጠኝ ተማሪዎች ደግሞ ከ500 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል ።
ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማስገባት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ቢሠሩም በፈተና ወቅት በተከሰተው የጸጥታ ችግር እና በተለያዩ ምክንያቶች ማሳካት አለመቻሉን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።
በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 60 ተማሪዎች ከ351 እስከ 625 በማስመዝገብ ሁሉም ተማሪዎች ማለፋቸው ይታወሳል።
የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቱ ከመዋለ ሕጻናት እስከ 12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ልጆችና በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የኾኑ የከተማዋ ነዋሪ ልጆችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝም የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!