
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው የኑሮ ውድነት ለማኅበረሰቡ ፈታኝ መኾኑ እየተስተዋለ ነው።
በክልሉ የሚታየውን የኑሮ ውድነት አሚኮ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ለመታዘብ ጥረት አድርጓል።
ሸማቾች እንደነገሩን የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ከመሄድ ውጭ የሚቀንስ ነገር የለውም ይላሉ።
እንደሸማቾች ገለጻ በመሠረታዊ ፍጆታ ግብይት የሚፈጸምባቸው እቃዎች በየለቱ ዋጋቸው እያሻቀበ በመሄዱ ኑሯቸውን ፈታኝ እንዳደረገባቸው ነው የሚገልጹት።
ይሁን እንጅ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ካስቀመጣቸው አሠራሮች መካከል የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በየቀበሌው እንዲቀርቡ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደኾነ ገልጸዋል።
ሸማቾቹ እንደሚሉት ችግሩን ለማቃለል አቅርቦቱ ጥሩ ቢኾንም የመቆራረጥ ሁኔታ እንደሚታይበትም ነው ያብራሩት።
በክልሉ ንግድ ቢሮ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ እና መሠረታዊ የንግድ እቃዎች አቀርቦትና ክትትል ጉዳ ይ ዳይሬክተር ታፈረ ይመር እንደነገሩን በክልሉ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ምርት እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
አቶ ታፈረ በክልሉ የሚታየውን የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች የዋጋ ንረት ለመከላከል በቀበሌዎች በኩል ለሱቆች እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጅ ወቅታዊው የጸጥታ ሁኔታ ለክልሉ የተመደበውን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንኳን ለማምጣት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያስገነዘቡት።
ስኳር እና ዶቄትን ገበያው በሚፈልገው መጠን እንዲገባ ለማድረግም አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነም ነው የነገሩን።
ንግድ ቢሮ የሸማቾች ሥራ ማኅበራትን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን፣ ድርጅቶችን እና ተቋማትን በመደገፍ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እየሠራም ነው ብለዋል።
ከሰሞኑም የንግድ ቢሮው ባለሙያዎች ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው ክትትል እና ቁጥጥር እያደረጉ የእርምት እርምጃ እየወሰዱ እንደኾነም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!