
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተገኘው ሠላም ኢንዱስትሪዎች ከገቡበት ተጽዕኖና ጫና አገግመው ምርት ወደ ማምረት ሥራ መመለሳቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ አጋጥሞ በነበረው የሠላም መደፍረስ የጸጥታ ኀይሉ ከሕዝቡ ጋር በጋራ በመኾን የታዩትን ችግሮች ለመቀልበስ ተችሏል፡፡
በዚህም በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ሠላሙ እየተመለሰ ነው፡፡ በጸጥታ ችግር ተገድበው የነበሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች አሁን በተሻለ ኹኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተገኘው ሠላምም ተጽዕኖ ውስጥ ገብተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ ተመልሰዋል፡፡
አሁን ላይ በተገኘው ሠላም ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል ያሉት ኃላፊው ኢንዱስትሪዎች የገጠማቸውን ችግሮች እንዲፈቱ ክልሉ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ባለሀብቶችም ተረጋግተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የማበረታታት ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በግጭቱ ከፍተኛ ተጽዕኖ የገጠማቸው ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የማበረታታት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በኢንዱስትሪዎች በኩል አሁን ላይ በተጨባጭ የታየው ችግር ያመረቱትን ምርት ወደ ተለያየ ቦታ መውሰድ አለመቻል እንደኾነም ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ምክክሮች ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡ በብዙ ቦታዎች የልማት ሥራዎች በተቻለ መጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ኅብረተሰቡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባትም ጥረት ተደርጓል፡፡
ኃላፊው እንዳሉት፤ በተለይም በምሥራቁ የክልሉ ክፍል ያሉት አካባቢዎች በአስተማማኝ ኹኔታ ሁሉም ነገሮች እየተስተካከሉና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ማኅበረሰቡ የተስተካከለ ኑሮ እየመራ ይገኛል፡፡
ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት ከትምህርት ጋር ተያይዞ አሁን ባለው ኹኔታ በበርካታ የክልሉ ከተሞችና ወረዳዎች ተማሪዎችን በመቀበል የማስተማር ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ይህም በመማር ማስተማር ሂደቱ ተማሪዎች እንዳይስተጓጎሉ የጸጥታ ኀይሉ በሠራው ሥራ የተገኘ ውጤት መኾኑን አመልክተዋል፡፡
ከጤና አኳያ በክልሉ የኮሌራና የወባ ወረርሽ መታየቱን የገለጹት ኃላፊው፤ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የዘመቻ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ረጂ አካላት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ድጋፍ ማድረግ መቻላውንም ጠቁመዋል፡፡ ክልሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ከግብርና ጋር ተያይዞ ሌሎች የልማት ሥራዎችም በበርካታ አካባቢዎች በአግባቡ እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው የግብርና ልማት ወደ ኋላ እንዳይመለስና ችግር እንዳይደርስ ሕዝቡ ጥረት እያደረገ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለሙያዎችም አርሶ አደሩን እየደገፉት እንዳሉና ልማቱ በከተማ የታጠረ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ የገጠር ወረዳዎች አርሶ አደሩን በመደገፍ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!