
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግ እና ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠርን ዓላማ አድርገው ከሚሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ከተመሠረተ ጀምሮ ለ4 ሺህ 792 ኢንተርፕራይዞች ማሽኖችን በዱቤ በማቅረብ ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ሃብት እንዲያፈሩ እያደረገ ይገኛል፤ ዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር።
በአክሲዮን ማኅበሩ ተጠቃሚ ከኾኑት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ደግሞ ቀለምወርቅ፣ ዘውዱና ጓደኞቻቸው ማኅበር አንዱ ነው። የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ቀለምወርቅ መላኩ እንዳሉት ማኅበሩ በ2009 መጨረሻ 20 ዶሮዎችን በማርባት ነበር ሥራ የጀመረው። 2010 ዓ.ም በክልሉ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ግን በሥራቸው ላይ ሳንካ ፈጠረ፡፡ የዶሮ መኖ ማቅረብ እጅግ ፈታኝ ችግር ኾኖ መጣ።
ችግር መፍትሔን ይወልዳል እንዲሉ የተቋረጠውን መኖ ችግር ለመቅረፍ የአካባቢያቸውን ጸጋ ተመለከቱ፡፡ በወፍጮ እና በሙቀጫ መኖ በማዘጋጀት የዶሮ እርባታውን ስጋትም ውስጥ ኾነው ገፉበት። ከራሳቸው አልፈው በዶሮ እርባታ ለተሠማሩ ጓደኞቻቸው ጭምር በማቅረብ ከኪሳራ ታደጓቸው።
ይህንን ጥረታቸውን የተመለከተ አንድ ሰው ሥራዎቻቸውን የሚያቃና አንድ ምክረ ሃሳብ ቸራቸው፡፡ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ማሰራት እኮ ይቻላል አላቸው። ምክረ ሃሳቡንም ተቀብለው በባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ መጠነኛ ማሽን በማሠራት በእጅ ይዘጋጅ የነበረውን መኖ በተሻለ መንገድ በማሽን ማዘጋጀቱን ቀጠሉበት።
የገንዘብ አቅማቸው እያደገ ሲመጣ ደግሞ በዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በብድር እንዲቀርብላቸው ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸው በጎ ምላሽን አግኝቶ እና ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ማሽኑን ተረከቡ፡፡
ማሽኑን ከተረከቡ ጀምሮ መኖ በሰፊው በማምረት ለአካባቢው እንስሳት አርቢዎች እና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እስከ አሁን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። መኖ በራሳቸው አቅም ማዘጋጀታቸው ከሌላ አካባቢ ለመኖ ግዥ ይወጣ የነበረውን ወጭ በግማሽ መቀነስ ተችሏል ይላሉ ወይዘሮ ቀለመወርቅ። በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ይቋረጥ የነበረው የምርት አቅርቦት ውስንነትም ተቀርፏል።
ውስን ኾነው የጀመሩት ዶሮ እርባታ ሥራ አሁን ላይ ለ30 ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ከጋሪ ሰራተኛ እስከ ከፍተኛ የጭነት አሽከርካሪዎች እና ባለሃብቶች ጭምር በሰንሰለቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በየዶሮ እርባታ የተጀመረው ጥረት እስከ መኖ ማቀነባበር ድረስ አድጓል፡፡ በ200 ብር የተወጠነው መነሻ ገንዘብ አሁን ላይ እስከ 30 ሚሊዮ ብር የሚገመት ካፒታል ማፍራት አስችሏል።
ወጣቶችን ወደ ሥራ ፈጣሪነቱ ዓለም ለማዋሃድ ግንዛቤ ፈጠራ ቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባ ወይዘሮ ቀለምወርቅ ይመክራሉ። ሥራ ፈጣሪነት መነሻ ካፒታል ብቻ ሳይሆን ትዕግስት እና ጽናትን ይጠይቃል፡፡ ሁልጊዜም ነገሮች አልጋ በአልጋ ኾነው አይሄዱም፤ ተስፋ አስቆራጭ ስጋት እና ቅስም ሰባሪ ክስረት የሥራ ፈጣሪነት ተጠባቂ ክስተቶች ናቸው፡፡ ዋናው ነገር ፈተናን በብስለት አልፎ ስኬታማ መሆን ነው፡፡
ከእያንዳንዱ ስኬታማ ሰዎች ጀርባ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች፤ አስደንጋጭ ሁነቶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ የሥራ መስክ የተሰማራ ወጣት ተነሳሽነት እና ተስፋ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለችግር የማይበገር እና ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ አመንጭ መኾን ካልቻለ ራስን መለወጥ እንደማይቻል ተሞክሯቸውን ነግረውናል። ጥረትን የሚያግዙ፤ ወረት የሚያስይዙ ልክ እንደ ዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ አክስዮን ማኅበር ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ሲገኙ ደግሞ ተጨማሪ አቅም አድርጎ መጠቀም ይገባል ይላሉ፡፡
በዋሊያ ካፒታል እቃ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር ጣና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ጋሻው አለሜ እንዳሉት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከሥራ ፈጣሪ ወጣቶች እና ኢንተርፕራይዞች ጋር ይሰራል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሦስት ቀበሌዎችን ጨምሮ በመሸንቲ እና መራዊ አካባቢዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን እና በአገልግሎት ዘርፎች የመንግሥትን አደረጃጀት ተከትለው ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ማሽኖችን እያቀረበ ይገኛል ብለውናል።
በ2015 በጀት ዓመት ለ50 ኢንተርፕራይዞች ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 387 ማሽኖችን ማሰራጨቱን በማሳያነት አንስተዋል። በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ለ90 ኢንተርፕራይዞች 90 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 315 ማሽን ለማሰራጨት በእቅድ ተቀምጧል።
ይሁን እንጅ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለፉት ሶስት ወራት ማሰራጨት የተቻለው ለ7 ኢንተርፕራይዞች ብቻ መኾኑን ነግረውናል። መንግሥት የሚታዩ የመሰረተ ልማት በተለይም ደግሞ የኃይል አቅርቦት ችግሮችን መፈታት ከቻለ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!