በምርት ዘመኑ የተሻለ ግብይት እንዲኖር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

37

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምርት ዘመኑ የተሻለ ግብይት እንዲኖር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

አማራ ክልል ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ይመረቱበታል፡፡ አርሶ አደሮች እና ባለሃብቶች ለገበያ በሚያቀርቧቸው ምርቶች ላይ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፡፡ ባለፈው የምርት ዘመን ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ በተፈጠረ ክፍተት ተጎጂ እንደነበሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ የሰሊጥ ግብይት ላይ አስቀድሞ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች እና ባለሃብቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑና ለተጨማሪ ምርት እንዲሠሩ የገበያ ትስስር ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ በገበያ ትስስር ዙሪያ ክፍተት ከተፈጠረ ባለሃብቶች እና አርሶ አደሮች ተስፋ እንደሚቆርጡም ገልጸዋል፡፡

የሰሊጥ ምርት ገበያ እንዳይቀንስና አልሚዎችን እንዳይጎዱ መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት የገበያ ትስስር ላይ በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡ ባለፈው የምርት ዘመን ማሾና አኩሬ አተር ላይ የገበያ ትስስር ችግር በስፋት እንደተስተዋለም አስታውሰዋል፡፡

በገበያ ትስስር ችግር ምክንያት ባለሃብቶች እና አርሶ አደሮች መጎዳታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የገበያ ትስስር ላይ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብልና ኢንዱስትሪ ምርት ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው ሐበሻ የሰሊጥ ምርት አስቀድሞ የገበያ ትስስር ያለው ምርት መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል አልፎ ለውጭ ገበያ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንደሚቀርብም ነው የተናገሩት፡፡ ውል የያዙ ነጋዴዎች ምርቱን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

በገበያ ትስስር ዙሪያ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ያለው የሰሊጥ ምርት ወጥ ኾኖ ግብይቱ እንዲፈጸም የማድረግ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

አዲስ ግብይት ከጥቅምት 30/2016 ዓ.ም በኋላ እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡ ምርቱ ቀድሞ እየደረሰ በመኾኑ ግብይቱ ቀድሞ የሚጀመርበት እድልም ሊፈጠር ይችላል ነው ያሉት፡፡

ግብይቱ በደንብና በመመሪያ እንደሚፈጸምም አስታውቀዋል፡፡ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጥታ ማቅረብ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡ አርሶ አደሮች በአካባቢው ለሚገኝ ነጋዴ ብቻ እንዲያቀርቡ ግዴታ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያበረታታው አምራቹን መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

ባለፈው ዓመት በማሾና በአኩሪ አተር ምርቶች ላይ የግብይት ችግር እንደነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ የሰሊጥ ግብይት ግን ጥሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በግብይት ላይ የነበረውን ችግር በመፍታት በምርት ዘመኑ የተሻለ ግብይት እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በግብይት ሰንሰለቱ መካከል የሚገቡ ጣልቃገቦች ግብይቱን እንዳይጎዱት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ የትኛውም ምርት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል እንደሚያልፍም ተናግረዋል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በውጭ ገበያ ግብይት ላይ እንደሚወሰኑ ያነሱት ዳይሬክተሩ የውጭ ገበያ በሚወድቅበት ጊዜ አርሶ አደሮች ተጎጂ እንደሚኾኑም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በአኩሪ አተር ላይ የነበረው የገበያ ችግር ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደኾነም አንስተዋል ባለሃብቶች ለውጭ ገበያ በቀጥታ ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቀዋል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት ግን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተመዝኖ እንደሚያልፍም ተናግረዋል፡፡ ደረጃና ጥራቱ እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መኖር ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሃብቶች በውላቸው መሠረት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ምርት እንዲገዙም አሳስበዋል፡፡

አርሶ አደሮች ምርታቸው ደረጃውን የጠበቀ ከኾነ በዋጋ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ነው የተናገሩት፡፡ አርሶ አደሮች ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡የምርት ጥራቱን ጠብቀው እስካመረቱ ድረስ ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ መስከረም 28/2016 ዓ.ም ዕትም
Next articleየዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ጀመሩ።