
ባሕር ዳር፡ መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደሬሽን ምክር ቤት ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ 6ኛ የፓርላማ ዘመን 3ኛ ዓመት የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
በስብሰባውም የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታን ጨምሮ የአምስት ቋሚ ኮሚቴዎች የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድንና የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን አጽድቋል፡፡
እቅዶቹን ካጸደቀ በኋላም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “የብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት” ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ለኢትዮጵያ እድገት ወጣቶች ያላቸውን የጎላ አበርክቶ በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታትና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከ18 እስከ 35 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች በፍላጎታቸው ብሔራዊ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው÷ ረቂቅ አዋጁ የወጣቶችን የዘመናት የተናጠልና የተደራጀ ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ሰነድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል አሻድሊ ሀሰን እና አወል ጀማቶ ረቂቅ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅና ተግባራዊ ሲሆን የጎላ ሀገራዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በፌደሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ሕገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ጌታሁን አብዲሳ ወጣቶች ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!