
ባሕር ዳር: ጥር 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) እስካሁን ከ23 ሀገራት 14 ሺህ 557 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አራት ሰዎች (አንድ ቻይናዊ እና ሶስት ኢትዮጵያውያን) በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው፣ አንድ በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡ ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁንም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው እንደተመላከተው የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታኅሳስ 21, 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ውሃን ግዛት የተከሰተ መሆኑን አሳውቋል፡፡ በድርጅቱ ሪፖርት መሠረትም በሽታው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 24/ 2012 ድረስ ከ 23 ሀገራት በጠቅላላ 14 ሺህ 557 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ከቻይና ውጪ ባሉ አገራት ደግሞ 146 ሰዎች ናቸው በቫይረሱ የተጠቁት፡፡
ከነዚህም ውስጥ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ፈረንሳይ፣ ኔፓል፣ ካናዳ፣ ማሌዥያ፣ ቬትናም፣ ካምቦዲያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሲሪላንካ፣ ፊንላንድ፣ ህንድ፣ ጀርመን እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ይገኙበታል፡፡ ሌሎች የመረጃ ምንጮች ደግሞ እስከ ጥር 25 ድረስ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ 17 ሺህ 373 ሰዎች መድረሱን፣ 362 ታካሚዎችም ህይወታቸው ማለፉን ዘግበዋል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
እንደ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስትር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛ፡፡ ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከልም ብሔራዊ ‹‹ታስክ ፎርስ›› እና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ሥራ መጀመራቸው ተጠቅሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አየር መንገድ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደተሰጠም ነው ተገለጸው፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ 200 ለሚሆኑ የሆስፒታል የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በጤና ሚኒስተር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥም ተገልጧል፡፡
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በ27 የተለያዩ የድምበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ይገኛል ብሏል ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው፡፡ እስከ ጥር 24/2012 ድረስ 47 ሺህ 162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ ተደርጎላቸው ከነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 695 ሰዎች የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሀገር ውስጥ በሚቆዩበትን ጊዜ፣ አድራሻ፣ እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝ እስከ 14 ቀን ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየተከታተለ ይገኛል ነው ያለው ሚኒስቴሩ፡፡
በኢትዮጵያም ከቻይና ውሃን ግዛት የመጡ እና የመተንፈሻ አካል ህመምና ከፍተኛ ሙቀት ማሳየት የጀመሩ ሁለት (2) ሰዎች እና ከእነርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ተጨማሪ ሁለት (2) ሰዎች ተገኝተው በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንና ናሙናቸውም ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን ጤና ሚኒስቴር ገልጧል፡፡ ጥር 21/2012 ዓ.ም የምርመራ ውጤቱ የደረሰና ሁሉም ናሙናዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ በዚያው ቀን ከለይቶ ማቆያ እንዲወጡ ተደርጓል ያለው ሚኒስቴሩ ይህንንም ተከትሎ ለቤተሰቦቻቸው ሲደረግ የነበረው ክትትል ተቋርጧል ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም አራት (አንድ ቻይናዊ እንዲሁም ሶስት ኢትዮጵያውያን) ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው አንድ በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነና ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጧል፡፡