
“የታማኝ ግብር ከፋዮች የምሥጋና እና የዕውቅና መርሐ-ግብር ሐሙስ ይካሄዳል”
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ”ግብር ለሃገር ክብር” የግብርና ታክስ ንቅናቄ አካል የኾነው 5ኛው ዙር የ2015 የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና መርሐ ግብር ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሤ “ግብር ትልቁ የኢኮኖሚ መሰረት እና የክብር ምንጭ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በ2022 ኢትዮጵያ ሀገራዊ ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለግብር ሕግ ተገዢ በመኾን የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዕውቅና መስጠት ያስፈለገበት ምክንያት እንደኾነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ተሸላሚ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለሀገራችን ንግድ መሳለጥ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት መበረታታት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ከ2011 ጀምሮ ለታማኝ ግብር ከፋዮች የምሥጋና እና ዕውቅና መርሐ ግብር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም በ5ኛው ዙርም ከ500 በላይ ለኾኑ ታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅናን ይሰጣል ተብሏል።
ኢቢሲ እንደዘገበው ጥቅምት 1 በሚካሄደው በዚህ የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ በተቀመጠው መመዘኛ መሰረት 50 የፕላትኒየም ተሸላሚ፣ 150 የወርቅ እና 300 የብር ተሽላሚዎች እንደሚኖሩም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!