በፍኖተሰላም እና ደብረማርቆስ ከተሞች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

62

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተሰላም እና ደብረማርቆስ ከተሞች ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ የሰላም እጦት የነበረ መኾኑ ይታወሰል፡፡ አሁን ላይ በእነዚህ ከተሞች በተገኘው አንጻራዊ ሰላም ነዋሪዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

የፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪዎች ግጭቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ከማድረሱ ባሻገር ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳጋለጣቸው አንስተዋል፡፡

ባልተረጋጋ ኹኔታ ውስጥ በመቆየታቸው ኑሮ ውድነቱ መባባሱን አንስተዋል፡፡ በከተማዋ የቀን ሥራ ሠርተው ቤተሰቦቻቻውን የሚያሥተዳድሩ ነዋሪዎች የበለጠ ተጎጅ መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል። የባንክ አገልግሎትም ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች እስካሁን አለመከፈታቸው በኑሯቸው ላይ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል። ከሳምንት በላይ ተቋርጦ የነበረው የስልክ ኔትወርክ መጀመሩ ደግሞ ሰላሙን ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎች፡፡

የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎችም ከተማው ወደ ሰላም በመምጣቱ ሱቆች፣ሆቴሎች፣ ባንኮች እና የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የሰላም እጦቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱ እንዳሳዘናቸውም ያነሳሉ፡፡

በርካታ ማኅበራዊ ተቋማት ውድመትን አስተናግደዋል ነው ያሉት፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሰላም ለአካባበቢው አስፈላጊ መኾኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ችግሩን በውይይት እና በምክክር መፍታት መቻል አለብን ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል። ጦርነት አውዳሚ እንጂ አትራፊ አይደለም፤ ይኽን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተቀመጠ ሕግና ሥርዓት መሠረት ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ይገባል ተባለ፡፡
Next articleከ2 ሚሊየን 8 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የወልዲያ ከተማ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።