
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከራእይ እና ተልእኮ ጎን ለጎን 12 የሥነ ምግባር እሴቶች ተከትበው እንመለከታለን፡፡ ተግባራዊ ይኾናሉ የተባሉ እሴቶች በመጣሳቸው ሰዎች በተለያዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ሲማረሩ ማየት የተለመደ ኾኖ መምጣቱን አሚኮ በተለያዩ ጊዜያት ከሚሠራቸው ዘገባዎች ጭምር መረዳት ይቻላል፡፡
ይህ ተግባር በሕግ አግባብ እንዴት ይታያል ስንል የሰሜን ሸዋ ዞን በፍታሐብሔር ዳኝነት አገልግሎት አሥተዳደር ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበራ ሸዋንግዛው ባነሳነው ጥያቄ መሠረት በተቀመጠ የሕግ ሥርዓት ለባለጉዳይ አገልግሎት አለመስጠት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኾናቸውን ነግረውናል፡፡
አገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ እና ከጥራት አንፃር ሊታይ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ገጥሞኛል የሚል የማኅበረሰብ ክፍል ወደ ፍትሕ የሚመጣ ከኾነ አገልግሎት ሰጭው የተቀመጠውን የሕግ ሥርዓት የጣሰ መኾኑ ከተረጋገጠ በዲስፕሊን ፣ በወንጀል እና በፍታሐብሔር ሕግ ተጠያቂ ይኾናል ብለዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት ከላይ እስከ ታች ያሉ መሪዎች የሕግ ሥርዓት ተከትለው ክትትል ማደረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
አቶ አበራ ችግሩ በቸልተኝነት እየታለፈ ለመልካም አሥተዳደር ችግር እየዳረገ እንደሚገኝም ያነሳሉ፡፡
ማኅበረሰቡ ችግሩን የፈጠሩትን በማጋለጥ ከተቋማቱ ጀምሮ የተጠያቂነት ሥርዓት በማስፈን አገልግሎት አሰጣጥ ችግርን መሻገር ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!