አዊዎች እንኳን ሰዎቹ ፈረሶቻቸውም በሀገረ መንግሥት ምስረታ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ባለቤቶች ናቸው፡፡

1096

ባሕር ዳር: ጥር 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ፈረስ እና ፈረሰኛ በአዊዎች ዘንድ የክብር እና ጀግንነት ምልክቶችም ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የበዛ ባህል፣ ተዝቆ የማያልቅ ትውፊት፣ ድብልቅ ማንነት፣ ቅይጥ እሴት እና በአንድ የሃገር በፍቅር፣ በመከባበር እና በመቻቻል የሚኖሩ ሕዝቦች ሃገር ናት፡፡ የተለያዩም ሆነው በአንድ መቆም እና ሃገርን በጋራ መገንባትን ያውቁበታል-ኢትዮጵያውያን፡፡

ለኢትዮጵያ አንድነት እና የዘመናት ታሪክ ካስማ እና ማገር ከሆኑ ሕዝቦች መካከል አዊዎች ታላቅ አሻራ እንዳላቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ የአገዎች የዘር ሃረግ ከዋግ ሹሞች ይመዘዛል፡፡ እንኳን ሰዎቹ ፈረሶቻቸውም በሃገረ መንግሥት ምስረታ ዘመን የማይሽረው የታሪክ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህ ቀደምት ሕዝብ ታሪኩን ለዘመናት ያሸጋግር ዘንድ አንድ ማኅበር አለው፡፡ “የ7 ቤት አገው ፈረሰኞች ማኅበር፡፡” ማኅበሩ ‘የ7 ቤት አገው’ የሚለውን ስያሜ ያገኘውም በአንድ ወቅት ከዋግ ኽምራ አካባቢ እንደመጡ ከሚነገርላቸው ‘አንኬሺ፣ ባንጂ፣ ዚጋሚ፣ አዚኒ፣ ኳኩሪ፣ ቻሪና ሚቲክሊ’ የተባሉ ሰባት ወንድማማቾች እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ተስማሚ፣ ለአደንም ምቹ መሆኑን የተገነዘቡት ወንድማማቾቹ በአካባቢው ቀርተዋል። ይህንን ታሪካዊ አመጣጥ ለመዘከር የተመሰረተው “የ7 ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር” 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከሰሞኑ (ጥር 23/2012 ዓ.ም) አክብሯል፡፡ በአዊዎች ዘንድ ፈረስ የተለየ ቦታ አለው፡፡

ሀገርን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ የነበረው ታሪክ የማይሽረው ውለታ እንዳለ ሆኖ፣ ፈረስ ለአዊዎች ለእርሻ፣ ለክብረ በዓላት እና ለሌሎች ማኅበራዊ ክዋኔዎች ማድመቂያ፣ ለመጓጓዣ፣ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ…ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ጭራቸውን ደግሞ ለልዩ ልዩ ጌጣጌጥ መሥሪያ ይገለገሉበታል፤ የገቢ ምንጭም ያደርጉታል፡፡ እናም አዊ እና ፈረስ በታሪክ ተለያይተው አያውቁም።

አዊዎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው ጎን ሆነው በሰማይ የመጣን ጦር በፈረስ ተጋፍጠዋል፡፡ በሰላም ወቅት ደግሞ አርሰውና ጎልጉለው ጎተራን ሙሉ ለማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡ በአዊዎች ምድር ከሰርግ እስከ መልስ ፍቅር በፈረስ ላይ ይከብራል፤ ይደምቃልም፡፡ አንቡላንስ በለሌበት በዚያ ዘመን ፈረስ አንቡላንስን ተክቶ አገልግሏል፡፡ ፈረስ በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ዳገቱን ወጥቶ ቁልቁለቱን ወርዶ ማጓጓዣ ሆኖም ያገለግላል። ሃዘን እና ደስታ በአገው ምድር ፈረስ ከሌለበት አይደምቅም፡፡

ፈረስ እና ፈረሰኛ በአዊዎች ዘንድ የክብር እና ጀግንነት ምልክቶችም ናቸው፡፡ አንድ ሰው ፈረሰኛ ለመባል ፈረስ፣ ኮርቻ፣ ፋርኒስ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ምቹና ግላስ ለፈረሱ ያስፈልገዋል። ለፈረሰኛው ደግሞ አለንጋ፣ ዘንግ፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጀበርና ሊያሟላ ይገባል። ጦር፣ ጋሻና ሌሎች የአባቶቻችን የዘመቻ ቁሶች ካሉት ደግሞ ይህ ይበልጥ ተመራጩ ነው።

የ7 ቤት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የብሔረሰቡን ትውፊት በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ከዓመት ዓመት ድምቀቱን እየጨመረ 80 ዓመታት የሞላው በዓሉ ለዘመናዊው መንግሥት መዋቅርም ተምሳሌት እንደሆነ እየተመሠከረለት ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Image may contain: one or more people and outdoor
Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥር 25-5-2012 ዓ/ም
Next articleአራት አዲስ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ መገኘታቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡