
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 በጀት ዓመት በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 500 ሺህ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ መታቀዱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸው (ዶ.ር) እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት 500 ሺህ ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገራት ሄደው እንዲሠሩ ይደረጋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ያላገኙትን ጨምሮ በሀገር ውስጥ በቂ የሙያ ሥልጠና ያገኙ ዜጎች በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሕጋዊ መንገድ ሄደው እንዲሠሩ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የቴክኒካል ቡድኑ መቋቋም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥናቶችን በማድረግ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለዋል። ይህም ለተቀመጠው እቅድ መሳካት ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ነው ያስረዱት።
የሥራ ስምሪቱ ከዚህ ቀደም ዘመናዊ ባልኾነ መንገድ ሲሠራበት እንደነበርም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ኢፕድ እንደዘገበው አሁን ላይ አሠራሩን በሀገር አቀፍ ደረጃ የማዘመን ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!