“በአማራ ክልል ከ496 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የለማ ሰሊጥ እየተሰበሰበ ነው” ግብርና ቢሮ

44

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የ2015/16 የምርት ዘመን የደረሱ ሰብሎች ስብሰባ ተጀምሯል፡፡ በክልሉ ካለው የሰብል ስብሰባ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘው ሰሊጥ ነው፡፡ በክልሉ ሰሊጥ በስፋት ወደሚመረትባቸው አካባቢዎች ለሰብል ስብሰባው የጉልበት ሠራተኞች እየገቡ ነው፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በአማራ ክልል 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 160 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡ በክልሉ የሰብል ሰብሰባ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ የሰብል አሰባሰብ ሂደቱ በጥሩ ደረጃ ላይ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በስፋት እየተሰበሰበ የሚገኘው ሰሊጥ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል 496 ሺህ 304 ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈኑንም አስታውሰዋል፡፡ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ አለው ተብሏል፡፡ በሰሊጥ ላይ የተሠሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥራዎች አርሶ አደሮችን እና ባለሃብቶችን ወደ ሰሊጥ ልማት እንዲገቡ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡

የሰሊጥ ሰብል ሽፋን ከፍ ማለት ለአማራ ክልል ታላቅ እድል መኾኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ከሰሊጥ ሰብል 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ የሰብል አሰባሰቡ ተስፋ ሰጪ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በተለይም ወደ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በርካታ ሠራተኞች እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛ እጥረት እንዳይገጥም ሁሉንም አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከሰሊጥ ሰብል ባለፈ የምግብ ገብስ እና ሌሎች የሰብል አይነቶች እየተሰሰበሰቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አሁን ያለው የአየር ንብረት ለሰብል ስብሰባው ምቹ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰብልን በወቅቱ መሰብሰብ አንደኛው የግብርና ተግባር መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በክልሉ ያለው የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ስርጭት ጅማሮ ተስፋ ሰጪ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ለሰብል አሰባሰቡ እገዛ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሰብልን መሰብሰብ ይገባልም ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ግብርናውን ለማዘመን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መልካም መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለቴክኖሎጂ አቅርቦት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ካለው የቴክኖሎጂ ፍላጎት እና ስፋት አንጻር በቂ ቴክኖሎጂ አለመቅረቡን ግን እንደውስንነት አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልል ያለው የሰላም እጦትም በግብርና ሥራው ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው የተናገሩት፡፡ ከአርሶ አደሮች ጋር እየተገናኙ ለመደገፍ የሰላም እጦቱ እንቅፋት መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ በሰብል አሰባሰብ ሂደቱ ላይም ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በችግር ውስጥ ኾነውም አስፈላጊውን ሥራ ሁሉ እየለዩ እየሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወቅቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ቀደም ብሎ ማዘጋጀት እና ማሰባሰብ የሚያስፈልግበት ወቅት መኾኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

የዘር ብዜት ላይም በልዩ ትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

አቶ አግደው የቀበሌ ባለሙያዎች በችግርም ውስጥ ኾነው አበረታች እና ተስፋ ሰጭ የኾነ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የጉልበት ሠራተኞች የሰሊጥ ሰብል በብዛት ወደ ሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች እንዲሄዱና ሰብል በወቅቱ እንዲሰበስቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ የምትጠብቀውን ውጤት ለማሰመዝገብ በቅንጂት መሥራት ያስፈልጋል” የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት
Next article“በ2016 የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 500 ሺህ ዜጎችን ለመላክ ታቅዷል” የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር