በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ይሰማራሉ ተባለ፡፡

27

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምቱ ወራት ብቻ እንዳይታጠር በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራትም ወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለማሳተፍ ታቅዷል።

በበጋው የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በክረምቱ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ተግባራትን ጨምሮ አዳዲስ ሥራዎችም የሚከናውኑ ይኾናል።

በተለይም ደግሞ የአረጋዊያን ቤት ግንባታና እድሳት፣ የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ፣ ሰብል ስብሰባ፣ ሊከሰት የሚችልን አንበጣ መከላከል፣ ግሪሳ እና መሰል ተባዮችን መከላከል፣ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ፣ በክልሉ ሰላም፣ በትምህርት፣ በጤና እና የመሳሰሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።

በመርሐ ግብሩ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ከ4 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል። በዚህም በመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሊተካ የሚችል ሥራ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል።

ወጣቶች በራሳቸው እውቀት፣ ጉልበት እና ጊዜ የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመግባባት ላይ የተመሰረተ የሥራ ስምሪት ይሰጣል ተብሏል።

የበጎ አድራጎት ሥራ ለወጣቶች ብቻ የተተወ እንዳልኾነ ያነሱት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተሾመ ፈንታው የክልሉን ልማት ለማፋጠን እና የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል መላውን ማኅበረሰብ የመሳተፍ ማኅበራዊ ግዴታ እንዳለበት አንስተዋል።

ለዚህ ደግሞ ወጣቶች፣ ተቋማት እና አደረጃጀቶች በባለቤትነት እንዲሠሩ ምክትል ኀላፊው ጠይቀዋል። በእውቀት እና በጉልበት ከሚደረግ አገልግሎት ባለፈ በገንዘብ ጭምር መደገፍ ይገባል ብለዋል።

ተግባሩ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜና አተገባበር እንዳለው ያነሱት ምክትል ኀላፊው በአማራ ክልልም አገልግሎቱን የተመለከተ ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መኾኑ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግሪሳ ወፍ ወረራ በተከተሰባቸው አካባቢዎች የተካሄደው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next article“በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ የምትጠብቀውን ውጤት ለማሰመዝገብ በቅንጂት መሥራት ያስፈልጋል” የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት