“የግሪሳ ወፍ ወረራ በተከተሰባቸው አካባቢዎች የተካሄደው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

41

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ ወረራ መከሰቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የግሪሳ ወፉን ወረራ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት መጀመሩንም አሚኮ ዘግቦ ነበር፡፡ በክልሉ የግሪሳ ወፍን ለመከላከል አሁንም እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች የግሪሳ ወፍ ወረራ መከሰቱንም አስታውሰዋል፡፡ የግሪሳ ወፉን ወረራ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኮሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑንም ነግረውናል፡፡

በክልሉ የግሪሳ ወፍ በተከሰተባቸው ዋና ዋና ቦታዎች ላይ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡ የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ከሆኑ ቦታዎች ላይም የኬሚካል ርጭት መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

የግሪሳ ወፉን ወረራ ከኬሚካል ርጭት ባለፈ በባሕላዊ መንገድም በመረባረብ መከላከል ይገባል ነው ያሉት፡፡ የኬሚካል ርጭት የሚያደርገው አውሮፕላን አንድ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ርጭት ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አውሮፕላኑ ወደ ሌሎች ክልሎች ለኬሚካል ርጭት እንደሚሄድም ተናግረዋል፡፡ አውሮፕላኑ ዳግም እስኪመለስ በባሕላዊ መንገድ ያለውን የመከላከል ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡

በአውሮፕላን የታገዘው የኬሚካል ርጭት ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ እርጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች 98 በመቶ በላይ ግሪሳውን የመግደል ውጤት እንደተገኘ ነው የተናገሩት፡፡

የሰላም እጦቱ በሰብል ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የግሪሳ ወፉን በመረበሽ እና ሌሎች ባሕላዊ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ልማትና ጥፋት መሳ ለመሳ ይዞ መጓዝ ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት እንቅፋት ነው” የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next articleበበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ይሰማራሉ ተባለ፡፡