
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ የጋራ ጉባዔ መክፈቻ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተዋል።
የያዝነው ዓመት ከ10 ዓመቱ የልማት እቅድ 2ኛው ምዕራፍ የሚጀመርበት ዓመት ስለመኾኑ ጠቁመዋል። በመኾኑም ያለፉትን ሦስት ዓመታት ጥንካሬዎችን ማስፋት እና የታዩ ውስንነቶችን ደግሞ ማረም አለብን ነው ያሉት።
“በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ዋነኛ ዓላማችን የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ማስቀጠል ነው” ሲሉም ገልጸዋል። “ልማት እና ጥፋት መሳ ለመሳ ይዞ መጓዝ ለዘላቂ ሀገራዊ እድገት እንቅፉት ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንቷ።
እንቅፋት የሚኾኑ ጉዳዮችን ማስተካከል እና የሀገራችንን እድገት ማፋጠን ለአፍታም የምንዘነጋው ጉዳይ አይኾንም ነው ያሉት። ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ የዚህ ዓመት የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና የሰላም አማራጮችን አሟጦ መጠቀም እንዲሁም ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ለማረጋገጥ መሥራት ነው ብለዋል።
የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥም በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል። “የሠላም በር ሁልጊዜም ክፍት ነው ፤ በተናጠልም ኾነ በጋራ በሰላማዊ መንገድ ከማንኛውም ወገን ጋር ለመነጋገር መንግሥት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።
የኃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ተግባራትን ግን መንግሥት አይታገሥም ነው ያሉት። በክፉም በደጉም ተሳስሮ ለዘመናት የኖረው ሕዝባችንን አብሮነት ለማላላት ብሎም ለመበጠስ በማለም የሚካሄዱ ዘመቻዎች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸውም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጠቁመዋል።
ይህ ከኢትዮጵያዊ ባሕል እና ሥነ ምግባር የወጣ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ለማቃቃር የሚሠራ የጥላቻ እና የሐሰት መረጃ የማሰራጨት ሥራ ለሕዝባችን አብሮነት አስጊ ነው ብለዋል።
በመኾኑም መንግሥት በመሰል እኩይ ድርጊት ላይ የተሰማሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ያከናውናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!