
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ6ኛው የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሀገሪቷ ርእሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ በ2016 ዓ.ም ምክር ቤቶቹ ትኩረት ቢሰጧቸው ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ርእሰ ብሔሯ ትኩረት ከሰጧቸው የትኩረት ነጥቦች መካከል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አንዱ እና ዋናው ነው፡፡
ትላንት ለነገ እንቅፋት መኾን የለበትም ፤ ትምህርት እንጂ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ እንዳይኾን መሥራት አለብን ብለዋል፡፡ እየተደማመጥን እና እየተመካከርን በራችንን ለሀሳብ እና ለምክክር ክፍት አድርገን እንጓዝ ፤ አንድነታችንን በማጠናከር ለሀገራችንን መጻዒ ተስፋ በጋራ መትጋት ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡
ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንን እና ኃይላችንን በነጋችን ላይ እናውል ያሉት ርእሰ ብሔሯ የዚህ ትውልድ ታላቁ ኅላፊነትም ይኽ ነው ብለዋል፡፡ ተግተን ከሠራን ከችግሮቻችን ወጥተን ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ያመላከቱ አበረታች ውጤቶችን እንደምናስመዘግብ ተመልክተናል ብለዋል ርእሰ ብሔሯ በንግግራቸው፡፡
በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ምክክር አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ መንግሥት ከየትኛውም ኃይል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንደኾነ ታይቷል ነው ያሉት፡፡
ተነጋግረን ላንግባባ እንችል ይኾናል ነገር ግን ጦርነት እና መሳሪያ መማዘዝ ፍጹም አማራጭ ኾኖ መቅረብ የለበትም ነው ያሉት፡፡ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ አሸናፊ እና ተሸናፊ ይኖራል ያሉት ርእሰ ብሔሯ “ውይይት ግን ሁሉን አሸናፊ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ያደሩ እና ለዘመናት የነበሩ የሀሳብ ልዩነቶች ለማስታረቅ እና ለማቀራረብ፤ ብሎም ወደ ተሻለ ሀገራዊ አንድነት እንዲወስደን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁመናል ብለዋል፡፡
የቀደሙ ዝንፈቶችን እና ክፍተቶችን በማረም ወደፊት እድላችንን ተመካክረን ማቅናት ይኖርብናል ሲሉም አክለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡ በተደጋጋሚ በታሪካችን ውስጥ እንዳመለጡን እድሎች ሁሉ ሀገራዊ ችግሮቻችንን በምክክር የምንፈታበት ይኽ እድል ግን ሊያመልጠን አይገባም ሲሉም የምክር ቤቶቹን አባላት አሳስበዋል፡፡
አንድ ክፉ ልማድ አለን ያሉት ርእሰ ብሔሯ እድሎች በእጃችን እንዳሉ በዋዛ እናሳልፋቸዋለን ፤ ከዘመናት በኋላ ግን እንቆጭባቸዋለን፡፡ ምክክሩ ያጠፋናቸውን ለማረም ፣ ያልተግባባነውን ለማግባባት ፣ የተሰበረውን ለመጠገን ፣ የተጣመመውን ለማቃናት ፣ የተራራቀውን ለማቀራረብ ፣ ዳር የቆመውን ወደ መካከል ለማምጣት እና ለሁላችንም የምትኾን ሀገር ለመገንባት መሠረት የምንጥልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነውም ብለውታል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹን አጠናቅቆ በዚህ ዓመት ወደ ምክክር ምዕራፍ ይሸጋገራል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነታችንን ማጥበቢያ እና አብሮነታችንን አጉልተን በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት ላይ የተስተዋሉ ስብራቶችን የምናክምበት ነው ብለዋል፡፡ የምክክር ሂደቱ የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጥሩ መደላድል ነውም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁላችንንም መስላ በሁላችን ልክ የተሠራች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፣ ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ዓላማ እና የተጣለበትን ሀገራዊ ኅላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የሁላችንንም ቀና ትብብር ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሁሉም ያገባዋል ፤ የምንነጋገረውም ስለሀገራችን እና ስለጋራ ቤታችን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!