“በ2015 ዓ.ም 547 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰራጭቷል” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

39

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ሀገራዊ እንቅስቃሴ በጉባዔው መክፈቻ ንግግራቸው ላይ አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቷ የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም ባለፉት 3 ዓመታት ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ስለመኾኑ አንስተዋል። የሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከፍተኛ መሻሻል ስለማሳየቱም ነው ያነሱት።

የባንኮች የብድር አሰጣጥ መጠን ስለማደጉም “በ2015 ዓ.ም ብቻ ከ547 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ተሰራጭቷል” ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ።

ዲጂታላይዜሽንን ከማስፋፋት አንጻር የፋይናንስ ዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም እያሳየ እንደኾነም ጠቁመዋል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሞባይል ዋሌት ተጠቃሚዎች መጠን ማደጉንም አመላክተዋል። በ2014 ዓ.ም 43 ነጥብ 32 ሚሊዮን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች የነበሩ ሲኾን በ2015 ዓ.ም ወደ 68 ነጥብ 36 ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥርም በ2014 ዓ.ም 16 ሚሊዮን 340 ሺህ የነበረ ሲኾን በ2015 ዓ.ም ወደ 27 ሚሊዮን 350 ሺህ ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።

በአጠቃላይ በዲጂታል ሥርዓቱ የተላለፈ የገንዘብ መጠንም በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲኾን በ2015 ዓ.ም ግን ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ በማለት ዘርፉ ለውጥ ማስመዝገቡን ፕሬዝዳንቷ በጉባዔው ላይ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለንግግር እና ለሰላም የሚረፍድ ጊዜ የለም” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
Next article“የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ እንዳይኾን እንሥራ” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ