
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተጀምሯል፡፡ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሀገሪቷ ርእሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እና የሀገራዊ ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ከእኛ ኢትዮጵያዊያን ምንም ነገር ሊጎድል አይገባም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በዚህ ትውልድ መካከል የለውጥ ፋና ተለኩሷል ያሉት ፕሬዚዳንቷ አዲስ የሁለንተናዊ ለውጥ ምዕራፍ ተከፍቷል ነው ያሉት፡፡ የተከፈተውን የለውጥ ምዕራፍ የተወሰኑ ዜጎች እና የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሳይኾን የመላው ኢትዮጵያዊያን የለውጥ ምዕራፍ አድርጎ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሀሳቦች ልንስማማም ላንስማማም እንችላለን ያሉት ርእሰ ብሔሯ ነገር ግን እድሉ የሀገር ፣ እድሉ የትውልድ መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የጎደለውን እየሞላን፣ ያነሰውን እየጨመርን፣ ያልተስማማንበትን እያቆየን፣ በተስማማንበት ላይ እየሠራን፣ በልዩነቶች ላይ ቆመን ሳንጋጭ፣ በተግባባንበት አብረን እየተጓዝን፣ ያልተግባባንበት ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ሲኖር ሕዝብ ተወያይቶበት እና የሕዝብን ድምጽ እያከበርን በመሄድ ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገር ልናስረክብ ይገባል ብለዋል፡፡
ዛሬ ላይ የምናያቸው የትኞቹም ያደጉ ሀገራት ልዩነቶች ሳይኖሯቸው ቀርቶ ሳይኾን ልዩነቶቻቸውን ከግጭት ባለፈ በጠረንጴዛ ዙሪያ ማየት በመቻላቸው ነው ለእድገት የበቁት ብለዋል፡፡ ልዩነትም አንድነትም የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው ያሉት ርእሰ ብሔሯ ዋናው ነገር ልዩነትን ጌጥ ፤ አንድነትን ደግሞ የአብሮነት ገመድ አድርጎ የማዋደድ እና የማስማማት ሥነ ልቦና መገንባቱ ነው ብለዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላም መፈታቱ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት ተምሳሌት ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከግጭት ወጥተን መልሶ ግንባታ ላይ ገብተናል ብለዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የታየውን የግጭት ኪሳራ እና የሰላም ትርፍ ማስላት ያስፈልጋል ፤ “ለንግግር እና ለሰላም የሚረፍድ ጊዜ የለም” ብለዋል፡፡
የተዋጊነት ሥነ ልቦና ከውጭ የመጣን ወራሪ ጠላት በመመከት ነጻነታችን ለማስጠበቅ አግዞናል ነገር ግን የሠለጠነ ሥርዓተ-መንግሥት ለመመስረት አልጠቀመንም ፤ የሠለጠነ ሥርዓተ መንግሥት ለመመስረት መመካከር፣ መወያየት፣ መነጋገር እና መከራከር ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ስኬታማ ለማድረግ ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን ምንም ነገር መጉደል የለበትም ሱሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!