“በተለወጠ ሀሳብ እና በተለወጠ ልቦና ልንነሳ ይገባል” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

28

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሁለቱ ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡ ርእሰ ብሔሯ በሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መጀመሪያ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው ለዘመናት የጸናችው እና ዘመናትን ያሳለፈችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ገጽታዎች አሏት ብለዋል፡፡ በአንድነት በርካታ መሰናክሎችን ተሻግረን ህልውናችንን አስከብረናል ፤ ተከባብረን እና ተሳስበን በአብሮነት ዘመናትን ተሻግረናል፡፡ ተባብረን፣ በአንድ ቆመን እና ዋጋ ከፍለን ሀገራችንን ለመውረር የመጡ ጠላቶቻችንን ድል ነስተን አሳፍረን ሸኝተናል ብለዋል፡፡

የታላላቅ ሥልጣኔዎች መገለጫ የኾኑ ትዕምርትን አንጸናል ያሉት ርእሰ ብሔሯ ለዓለም ሕዝብ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ሕግን፣ የእህል ዘሮችን እና ተቋማትን አበርክተናል ነው ያሉት፡፡ የነጻነት ተምሳሌት በመኾን እና አንገዛም በማለት ለመላው የጥቁር ሕዝብ የአርበኝነት ተምሳሌት ኢትዮጵያዊያን ቀደምቶቻችን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን አሉ ርእሰ ብሔሯ በንግግራቸው ራሳችንን አንድ አድርጎ የሚያግባባ ትዕምርት አጥተናል፡፡ ሁላችንም ሊያሰባስብ የሚችል ትርክት መገንባት ተስኖናል፡፡

በአብዛኞቻችን ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባት ተስኖናል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው እርስ በእርስ ተከፋፍለን እና ልዩነቶችን ማቻቻል ተስኖን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት በመግባት እንደ ሀገር የማይተካ ዋጋ ከፍለናል፤ አሁንም እየከፈልን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡ ሀገራዊ ጸጋዎቻችን በአግባቡ መጠቀም ተስኖን በድህነት ማቅቀናል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ባለሁለት መልኮች ሆነናል ነው ያሉት፡፡

አንዱ መልካችን ያለንን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ መልካዓ ምድራዊ እና መንፈሳዊ ጸጋዎች የሚያሳይ መልካችን ነው ያሉት ርእሰ ብሔሯ ሌላኛው መልካችን ግን ይህንን እድላችን እና ጸጋችን የሚያቀጭጨው እና ራሳችንን በራሳችን ያወደምንበት መልክ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የተቃርኖ ገጽታዎቻችን ማረም አለብን ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አሁን የመጣንበትን መንገድ ቆም ብለን የምንገመግምበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ ያተረፍነውን እና ያጎደልነውን ማስላት አለብን ነው ያሉት። ያተረፍንበትን ማጉላት፤ ያጎደልንበትን ደግሞ በሌላ መተካት ወቅቱ የሚጠይቀው ጊዜ ነው፡፡ “በተለወጠ ሀሳብ እና በተለወጠ ልቦና ልንነሳ ይገባል” ብለዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባዔ መካሄድ ጀመረ።
Next article“ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱ ጠቅላላ የሰብል ምርት ወደ 639 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ አስችለናል” ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ