“የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች 5ቱ ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ ችለዋል” ትምህርት ሚኒስቴር

125

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2015 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 50 በመቶ የማለፊያ ነጥብ አምጥተው ያለፉ ተማሪዎች 3 ነጥብ 2 በመቶ መኾናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

የትምህርት ሚኒሰቴር የ2015 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።

ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ 845ሺህ 188 ተማሪዎች መካከል 27ሺህ 267 ብቻ የሚኾኑት የማለፊያ ነጥብ ማምጣታቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል።

ዘንድሮ በተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት ኾኖ የተመዘገበው 649 ሲኾን በማኅበራዊ ሳይንስ 533 መኾኑም ተገልጿል።

3ሺህ 106 በመላው ሀገሪቱ ያሉ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና አስፈትነዋል። ከዚህ ውስጥ 1ሺህ 328 የሚኾኑት አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ 5 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍቸውን ተናግረዋል። የተሻለ ውጤት ከተመዘገበባቸውና ተማሪዎቻቸውን በሙሉ ማሳለፍ ከቻሉት መካከል ፦

👉በደብረ ማርቆስ የሚገኘው የክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ፣

👉በደሴ የሚገኘው ይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እና

👉በባሕርዳር የሚገኘው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ከባለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ ከስርቆትና ኩረጃ የፀዳ እንዲኾን ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት እንደነበርና ደንብና ሥርዓትን አክብሮ ከመፈተን አንፃር መሻሻሎች የታዩበት እንደነበር ተነስቷል።

ተማሪዎች ከመስከረም 29/2016 ዓ.ም ጀምሮ ውጤታቸውን በበይነመረብ ተጠቅመው በቀጥታ መመልከት እንደሚችሉም ተገልጿል።

የ2016 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ግንቦት ወር ላይ ይሰጣልም ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበበጀት ዓመቱ ለተሻለ ሥራ አፈጻጸም ዝግጅት ማድረጉን የሰሜን ሽዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
Next article6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባዔ መካሄድ ጀመረ።