
ደብረ ብርሃን: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 በጀት ዓመት ለተሻለ ሥራ አፈጻጸም ዝግጅት ማድረጉን የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እና በሰሩ ያሉ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ከ2013 እስከ 2015 ባሉት የበጀት ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት በተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ኾነው ነበር።
የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወካይ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ወንድሙ እንዳሉት በ2013 በጀት ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱ ለፍርድ ቤቶች ሥራ ትልቅ እንቅፋት ነበር።
በ2014 በጀት ዓመት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና በ2015 በጀት ዓመት ያጋጠመው የሰላም እጦት ጫና ፈጥሮ አልፏል ነው ያሉት። በፈተና ውስጥም ኾነው ግን የተሻለ አፈጻጸም እንደታየ ተወካይ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
በሦስት ዓመታት ወደ 202 ሺህ 384 የወንጀልና የፍታብሔር መዝገቦች ለወረዳ ፍርድ ቤቶች ቀርበዋል። ከእነዚህ መካከል 198 ሺህ 854 መዛግብት ውሳኔ የተሰጣቸው ሲኾን 3 ሺህ 530 መዝገቦች ወደ 2016 በጀት ዓመት ተላልፈዋል ብለዋል።
ተወካይ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉትም በ2016 በጀት ዓመት ተገልጋዮችን ይበልጥ ለማርካት የሚሠራ ይኾናል። ለዚህም በየጊዜው ክፍተቶችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ መታቀዱን አመላክተዋል።
ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በመገምገም ለቀጣይ ሥራ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ውይይት በደብረብርሃን ከተማ ተካሂዷል።
ፍትሕን በማስፈን ሂደቱ ሕጋዊ ማእቀፎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ውስጣዊ አሠራሮችን በማሻሻል የተሳካ ሥራ ለማከናወን የተደረጉ ጥረቶች በጥንካሬ ተነስተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አጋር አካላት በሰጡት አስተያየትም የፍርድ ቤቶች ሥራ ባመዛኙ መልካም የሚባል እንደኾነ አንስተዋል።
የተንከባለሉ ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ፣ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጠናከርና ሌሎች ቢሠሩ ያሏቸውን ሀሳቦችም አጋርተዋል። ለውጤታማነቱ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ እንደሚሠሩም ነው ያረጋገጡት።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!