“እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልጁ እንኳን ለ60 ቀናት ለ60 ሴኮንድ ‘አስደንጋጭ ቦታ ውስጥ ነው’ ሲባል ሊሰማው የሚችለው ስሜት ለታገቱት ተማሪዎችም ሊኖረው ይገባል፡፡” ኦባንግ ሜቶ

335

ባሕር ዳር: ጥር 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ለታገቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምጽ ሊሆናቸው እንደሚገባ አቶ ኦባንግ ሜቶ ጠየቁ፡፡

መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የዜጎችን ኅልውና ሊያስጠብቅ እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራች አቶ ኦባንግ ሜቶ ጠይቀዋል፡፡ 80ኛ ዓመት የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ክብረ በዓልን ከሰሞኑ በእንጂባራ ከተማ የታደሙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሥራቹ አቶ ኦባንግ ሜቶን አብመድ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን እገታ ያወገዙት አቶ ኦባንግ “የታገቱት ልጆች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከብሔር አጥር በመውጣት በሠላማዊ መንገድ ድምጽ ሊሆናቸው ይገባል” ብለዋል፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡ ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲላኩ በሚያገኙት እውቀት ሀገራቸውን ለመጥቀም እንጂ ለሌላ ዓላማ ስላልሆነ “የፖለቲካ መጠቀሚያ” መሆን የለባቸውም ብለዋል አቶ ኦባንግ ሜቶ፡፡ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልጁ እንኳን ለ60 ቀናት ለ60 ሴኮንድ ‘አስደንጋጭ ቦታ ውስጥ ነው’ ሲባል ሊሰማው የሚችለው ስሜት ለታገቱት ተማሪዎችም ሊኖረው ይገባል” ሲሉም ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በብሔር የተከለለው ህገ መንግሥት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጠሩት ችግሮች መንስኤ ነው ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሥራቹ ችግሮችን ለመከላከል በቅድሚያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መቆም እንዳለበት ነው የጠየቁት፡፡ “እንዲህ ዓይነት ከኢትዮጵያዊነት እሴት ጋር የሚጣረስ ድርጊት ሲፈፀም መንግሥት በፍጥነት እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል አለበት” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ህግ አለማስከበር ትናንት የተዘራው ዘረኝነት እጅግ እንዲባባስ ስለሚያደርግ መንግስት አሁንም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመሥራት የዜጎችን ኅልውና ሊያስጠብቅ እንደሚገባም ነው አቶ ኦባንግ ያሳሰቡት፡፡ “በዚህ ዘመን መለያችን ብሔር ሳይሆ ኅሊናችን መሆን አለበት፤ ኅሊና ያለው ሰው ከእራሱ አልፎ ለሌላ ሰው መኖር ይችላል” ያሉት አቶ ኦባንግ ሁሉም ዜጋ ህግ እንዲከበር አስተዋጽዖ በማበርከት አሁን በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡

ለግጭቶች እና ለችግሮቹ መንስዔ የሆነውን ህገ መንግስት ማሻሻል ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Image may contain: 1 person
Previous articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳድር ነዋሪዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን የእገታ ድርጊት አወገዙ፡፡
Next article“ቦርዱ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ግዴታ ለመፈፀም ከማንም ይሁንታ ማግኘት የለበትም፡፡” የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ