
ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ እየተባለ ለሚጠራው የቱሪዝም ማዕከል የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ተፈጥሯዊ ፀጋዎቿ በርካታ ናቸው፡፡ የዓለማችን ረጂሙ ወንዝ ከምንጩ የሚነሳባት እና በኢትዮጵያ ታላቅ ከሚባለው የጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኘው ባሕር ዳር ለጎብኝዎች እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ምቹ የኾነች ከተማ ናት፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው የቱሪዝም እንቅስቃሴ አሁንም ድረስ መፍትሔ ያልተገኘለት የሰላም እጦት ችግር ዘርፉን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ ይህን ችግር ለመሻገር እንደ ባሕርዳር ከተማ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚደግፉ በርካታ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኅላፊዎች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው የኢንዱስትሪ ፣ ፋብሪካ እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን የግንባታ ሂደቶች ተመልክተዋል፡፡ በቢአይካ ኮንስትራክሽን ድርጅት እየተገነባ ያለውን ጣና ማሪና ባሕር ዳርን የጎበኙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ ዘመናዊ ግንባታዎች የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይደግፋሉ ብለዋል፡፡
ከተማዋ ተፈጥሮ አብዝቶ ያደላት እና በርካታ ጸጋዎች ያሏት ውብ ከተማ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “ባሕር ዳርን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ አልመን እንሠራለን” ብለዋል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ፣ የከተማዋን ጸጋዎች በቀላሉ የሚጠቀሙ፣ ለጣና ሐይቅ ደኅንነት ሥጋት የማይኾኑ እና ከአካባቢ ብክለት ስጋት ነጻ የኾኑ የልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
ቢአይካ ኮንስትራክሽን ደርጅት እያስገነባው ያለው ጣና ማሪና ባሕር ዳር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመኾን አልፎ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው መዘመን ታስቦ የሚሠራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ ከተማዋ ከጣና ሐይቅ የምታገኘውን ነፋሻማ አየር የማይከልል እና ለሐይቁ ስጋት የማይኾን ፕሮጀክት መኾኑ ተመራጭ እንደሚያደርገውም አንስተዋል፡፡ ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት መኾኑ ደግሞ ብዙ ልንማርበት የሚገባ ነው ተብሏል፡፡
በከተማዋ የሚስተዋለውን የግንባታ ግብዓት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በከተማዋ ውስጥ የብረት ፋብሪካ መኖሩንም አንስተዋል፡፡ ፋብሪካው የከተማዋን እና የክልሉን የግንባታ ብረት ፍላጎት የሚያሟላ መኾኑ ችግሩን በቀጣይ ያቃልለዋል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ግንባታ ተጠናቅቆ ምርት የሚጀምሩበት ጊዜ ሩቅ ባለመኾኑ የሚስተዋለው እጥረት መፍትሔ ያገኛል ብለዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ እስከተቻለ ድረስ ባሕር ዳር የዓለም አቀፉ ቱሪስት መዳረሻ ትኾናለች ነው ያሉት፡፡
ባሕር ዳርን የዓለም አቀፍ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የከተማዋን ሰላም ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ ሰላም ለቱሪዝም መሠረት በመኾኑ ለከተማዋ ሰላም በጋራ እንሠራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!