“በወጣቶች በጎ አድራጎት ሥራ ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ችለናል” የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

36

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተሾመ ፈንታው ከሐምሌ1/2015 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ ከ4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶች በሦስት ወራት ውስጥ ካከናወኗቸው ሥራዎች መካከልም፦

✍️ 1 ሺህ 773 ቤቶች በአዲስ ተገንብተው 7 ሺህ 197 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ኾነዋል።

✍️ 2 ሺ 794 ነባር ቤቶችን በመጠገን 10 ሺህ 275 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

✍️ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ83 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን የማዕድ ማጋራት ሥራ ተሠርቷል።

✍️ በክልሉ በሚገኙ 610 ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷል፤ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ የመቀየር ሥራ ተሠርቷል፤ 71 ሺህ 290 ደርዘን ደብተር በማሰባሰብ ለተቸገሩ ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል።

✍️ ከ1 ሚሊዮን 256 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት 519 ሚሊዮን ችግን ተተክሏል ብለዋል ኀላፊው።

ከዚህም ባለፈ ሰብልን በመሥመር በመዝራት፣ የአቅመ ደካማዎችን እርሻ የማረስ እና ሰብላቸውን የመንከባከብ ሥራ መሠራቱን ነግረውናል።

የደም ልገሳ፣ የወባ መራቢያ ቦታዎችን ማዳፈን እና ማፋሰስ ትኩረት የተደረገባቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክረምቱ ወራት በወጣቶች በተሠራው ሥራ በመንግሥት ሊወጣ የሚችለውን ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት።

በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ሥራውን ለመከወን ትልቅ ችግር ቢኾንም ይህንን ተቋቁሞ አበረታች ተግባር ማከናዎን መቻሉን ቢሮ ኀላፊው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዛሬ ይከፈታል።
Next article“ባሕር ዳርን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ አልመን እንሠራለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው