
ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ ፋብሪካዎችን እና የአገልግሎት ዘርፎችን የግንባታ ሂደቶች ተመልክተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በተመራው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጉብኝት የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የግንባታ ዘርፉን ማዘመን የክልሉን ሁለንተናዊ የመልማት ፍላጎት መደገፍ ነው ብለዋል።
በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት ተቋማት የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከወጭ የሚገባውን ግብዓት እና ምርት እየቀነሱ ነው ብለዋል። በጉብኝቱ የተመለከቷቸው ተቋማት 40 በመቶ ከውጭ የሚገባውን ጥሬ እቃ በሀገር ውስጥ ምርት እና ግብዓት መተካት መቻላቸውን ነው ዶክተር አሕመዲን የጠቆሙት።
በክልሉ በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ 4 ሺህ 100 ገደማ ተቋራጮች እና 400 የሚደርሱ አማካሪ ድርጅቶች እንደሚገኙ የጠቆሙት ኀላፊው የእነዚህን ተቋራጮች እና አማካሪ ድርጅቶች አቅም ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
የግንባታ ዘርፉን በማዘመን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋለውን መጓተት እና የጥራት ደረጃ መቀነስ ችግሮች ለማረም እየተሠራ እንደኾነም ዶክተር አሕመዲን አንስተዋል።
“የግንባታ ዘርፉ የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን በኩል ሚናው አይተኬ ነው” ያሉት ዶክተር አሕመዲን የክልሉ መንግሥት እና አልሚ ባለሃብቶች የጀመሯቸውን ትልልቅ ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ የክልሉ ሰላም መኾን እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዶክተር አሕመዲን የክልሉን ሰላም በአጭር ጊዜ ለመመለስ እና በሙሉ አቅም ወደ መደበኛ የልማት ሥራዎች ለመግባት የሁሉንም የክልሉን ሕዝብ ቀና ትብብር እና ድጋፍ ይጠይቃል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!