
ባሕር ዳር: መስከረም 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የተመራ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊች ቡድን በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የግሉ ዘርፍ ታላላቅ የኢንዱስትሪ መዳረሻዎን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ቡድን በጉብኝቱ ከተማዋ ባላት ፀጋ ልክ ኢንቨስትመንቷ እንዲነቃቃ ተከታታይ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሀሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኅላፊን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች እና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሥራ ኅላፊዎች በምልከታው ተገኝተዋል፡፡
በቢአይካ ጠቅላላ የንግድ ሥራዎች ኅላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኮከብ ኢንዱስትሪ ግራናይት ፋብሪካን የተመለከቱት የክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በጉብኝቱ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እንደተመለከቱ ነግረውናል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ቢአይካ የተሰጠውን ቦታ በአግባቡ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀም የንግድ ድርጅት መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡ የፍብሪካዎቹ የግቢ ውበት እና የመሬት አጠቃቀም ሥርዓቱ ለሌሎቹ ኢንቨስተሮች ሞዴል መሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው የምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ምልከታ የግብዓት አጠቃቀም ሰንሰለት ሳይንሳዊ የንግድ ሥርዓትን የተከተለ እና ከሀገሪቱ እድገት ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የተነሳው የቢአይካ የንግድ ሥራዎች ድርጅት ሀገራዊ እና ክልላዊ አበርክቶ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን እና ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካቱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ለሀገር እና ከፍተኛ የሥራ እድል በመፍጠር ለዜጎች ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ የተነሳው እና አራተኛው ምልከታ ለሌሎች የግል ድርጅቶችም ተሞክሮ የሚሆነው የሠራተኞች አያያዝ ነው፡፡ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ባይካም ከሌሎች የግል ድርጅቶች የተሻለ የሠራተኛ አያያዝ እና የክፍያ ሥርዓት እንዳለ ከሰራተኞቹ በግሌ አጣርቻለሁ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ይኽ በጎ ተሞክሮ በሌሎችም መስፋት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
ኢንቨስትመንት የተረጋጋ እና ምቹ ከባቢን ይፈልጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ “አሁን ያለውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በፍጥነት ቋጭተን ወደ ልማት ካልገባን የሚደርሰው ኪሳራ ብዙ ነው” ብለዋል፡፡ የተለየ ፖለቲካዊ እሳቤ ያለው ቢኖር እንኳን በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብሎ በስክንነት መወያየት እንጅ የበርካታ ዜጎች የኑሮ መሠረት የሆኑ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚቆሙበትን አውዳሚ መንገድ መከተል እና መምረጥ የለብንም ብለዋል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ሕዝቡ ከምንም በላይ ሰላም ይፈልጋል፤ ሰላምም እንደሚያስፈልገው ያውቃል፤ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነትም በተገኘው አጋጣሚ አሳይቷል ብለዋል፡፡ በቀጣይም የክልሉ መንግሥት ለሀገር እና ለዜጎች መጠነ ሰፊ ፋይዳ ያላቸውን ኢንቨስተሮች በመሳብ የሥራ እድል ፈጠራና እና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!