“አፄ ቴዎድሮስ የሚማጸኑበት፣ ሁልጊዜም የሚመኩበት”

45

ባሕር ዳር: መስከረም 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኃያሉ ንጉሥ ይመኩበታል፣ ከዙፋናቸው ወርደው፣ ዘውዳቸውን አውልቀው፣ በትረ መንግሥታቸውን ጥለው ይሰግዱለታል፣ ኪዳን ያደርሱበታል፣ ቅዳሴ ያስቀድሱበታል፣ ኃይሉን ብርታቱን፣ ጥበቡን እና ጸጋውን ይሰጣቸው ዘንድ ይማጸኑበታል፡፡ ስሙ የሚመሰገንበትን፣ ክብሩ የሚገለጥበትን፣ ስጋና ደሙ የሚፈተትበትን ቤተ መቅደስ ያንጹለታል፡፡

ኃይል በእርሱ እንደሆነች፣ ጸጋና ሞገስም ከእርሱ እንደተቸረች፣ ጥበብ እና መወደድም ከእርሱ ዘንድ እንዳለች ያውቃሉና ጥበብ እንዲሰጣቸው፣ ኃይላቸውን እንዲያበረታቸው፣ መንገዳቸውን እንዲያቀናላቸው፣ ዘመናቸውን እንዲያሳምርላቸው፣ ዘውዳቸውን እንዲጠብቅላቸው፣ ራዕያቸውን እውን እንዲያደርግላቸው ያለ ማቋረጥ ይጠይቁታል፡፡ ለዳዊት ኃይልን፣ ለሰለሞን ጥበብን፣ ለነገሥታት ግርማና ሞገስን የሰጠው አምላካቸው ለእርሳቸውም እንዲሰጣቸው፣ የሚወዷትን ሀገራቸውን በዓለሙ ፊት ኃያል እንዲያደርጓት ጽናቱን እንዲያድላቸው ያለማቋረጥ ይነግሩታል፡፡

አብዝተው የሚወዷትን፣ ከነብሳቸው አስበልጠው የሚያፈቅሯትን፣ ያላቸውን ሁሉ የሚሰጧትንና የሰጧትን ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው፣ ጠላቶቿን ልብ እንዲሰጥላቸው፣ ፈጥኖም እንዲያስገዛላቸው፣ ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት እንዲያደርግላቸው በሰርክ ይለምኑታል፣ በልባቸው ውስጥ ላፍታም ሳያወጡ ያስቡታል፣ ይማጸኑታል፡፡

መርጦ፣ ለቅብዓ መንግሥት አዘጋጅቶ፣ በትረ መንግሥት አስጨብጦ፣ በእንቁ ባጌጠ የክብር ካባ አስጊጦ፣ በተዋበ ዘውድ አሳምሮ በአባቶቻቸው ዙፋን ላይ ያስቀመጣቸው የእርሱ እርዳታ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይሄንም በአደባባይ ይገልጣሉ፣ ደምዳቤ ጽፈው በላኩም ጊዜ የእርሱን ስም በመጀመሪያም በመጨረሻም ያነሳሉ፡፡ ኃያሉ ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ በዘመናቸው ከታቦተ መድኃኔዓለም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት፣ የጠበቀ አቅርቦት እና ፍቅር ነበራቸው ይባላል፡፡

ወደ ዘመቻ ከመሄዳቸው አስቀድሞ በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ኪዳን ያደርሳሉ፣ ያስቀድሳሉ፣ ኃይልና ብርታትን እንዲሰጣቸው፣ ሀገራቸውን አብዝቶ እንዲጠብቅላቸው ይማጸናሉ ይሏቸዋል፡፡ ቴዎደሮስ የዙፋናቸው መቀመጫ፣ የራዕያቸው መግለጫ አድርገዋት በነበረችው በደብረ ታቦር የመድኃኔዓለምን ቤተክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያኑም የተገባው ሁሉ ይሆንለት ዘንድ ስርዓት ሠርተዋል፡፡ የእርሳቸው አሻራ እና ስምም በቤተክርስቲያኑ ጎልቶ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ እርሳቸው በሀገራቸው የሠሩት እና ሊሠሩ ያቀዱት፣ ተስፋም የሰነቁበት ሁሉም በአምላካቸው እርዳታ እንደተፈጸመ፣ በአምላካቸው እርዳታም እንደሚፈጸም ያውቃሉ፡፡

ተክለጻዲቅ መኩሪያ አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት መከራ ገጥሟት የነበረችን ኢትዮጵያ ወደ ነበረ ክብሯ ለመመለስ የታተሩ፣ ዘመነ መሳፍንትን የቋጩ፣ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ማዕከላዊ መንግሥት የደከሙ ታላቅ ንጉሥ እንደነበሩ ጽፈዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንት ቋጭተው፣ የኢትዮጵያን እንድነት መሠረት ባያስይዙና ማዕከላዊ መንግሥትን በማይመልሱ ኖሮ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ባሁኑ ወርድና ቁመቷ ከእነ ሀብቷ አናገኛትም ነበር ብለዋል በታሪክ መጻሕፋቸው፡፡

ሁሉም በየቤቱ ማን ከማን ያንሳል አሻፈረኝ እያለ እርስ በእርሱ ሲዋጋ ለቅኝ ገዢዎች ጥርጊያ ጎዳና ይከፍት ነበር፡፡ ከእርሳቸው በኋላ የመጡ ነገሥታት በስልጣን ተደላድለው መጠናከር ያገኙት በቅድሚያ የዳንዴዎችን መሳፍንት ቅስም ቴዎድሮስ ሰባብረው የመከፋፈሉን መርዝ ከነቀሉ በኋላ በመሆኑ ነው፡፡ ቴዎድሮስ የጠረጉት የአንድነት ጎዳና ለተከታዮቻቸው ቀለል ያለ የመንደርደሪያ መስክ ሆኗል ብለዋል ተክለጻዲቅ፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ሀገራቸውን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ ለክብሯና ለማዕረጓ ይመጥናል ያሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ለሀገር ክብር ሲባል ራሳቸውንም ሳያወላውሉ ሰውተዋል፡፡ በዚህም አድራጎታቸው ለሕዝባቸው የጀግንነት እና ኩራት ሲያወርሱ፣ በተለይ በጠላቶቻቸው በእንግሊዝና በጠቅላላው በውጭ ሀገር ሰዎች ዘንድ መገረምን አሳድረው፣ የወደፊት ታሪካቸውን ተደናቂ እንዲሆን አድርገውታል ይላሉ የታሪክ ጸሐፊው ተክለጻዲቅ፡፡

ተክለጻዲቅ ስለ ቴዎድሮስ ሲጽፉ “ አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መንግሥታቸው በታላቅ የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በአማረ አዳራሽ ተቀምጠው፣ ዘውድ ደፍተው፣ በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ በዙፋን ላይ ተንሰራፍተው፣ በወርቅ አልጋና በሚደላ ፍራሽ ላይ ተጋድመው፣ የዚህን ዓለም ንጉሣዊ አዱኛ ማጣጣም ሳያምራቸው፣ ለራሳቸው ባርኔጣ፣ ለእግራቸው ጫማ ሳይፈልጉ ያለ ምንም እረፍትና መዝናናት በድንኳን እየኖሩ፣ በከብት ጀርባና በእግራቸው ከአውራጃ ወደ አውራጃ በመዘዋወር፣ ዳገት ቁልቁለቱን፣ ሸለቆና ወንዛወንዙን፣ በማቋረጥ ቆንጥር ለቆንጥር በክረምትና በበጋ በመንከራተት እየታገሉ አዲሱን የመሬት ሥሪትና የማዕከላዊ መንግሥትን አቋም በማሳመን፣ ከመሳፍንትና ከካህናት ጋር በመከራከር የውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሀገራቸውን ሰው እንዲያሰለጥኑላቸው በመጨቃጨቅ ጉልበታቸውንም፣ አዕምሯቸውንም፣ በመጨረሻ ሕይወታቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለሚወዷት ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የሥልጣኔና የአንድነት ሕይወት ሰውተዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነትና ውሕደት የሚወድ ያሁኑም የወደፊቱም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይሄን ውለታ ተገንዝቦ የእኚህን ንጉሥ ስማቸውን በአክብሮትና በአንድናቆት ሊዘክረው ይገባል” ብለዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በመቅደላ ተራራ ላይ በክብር ራሳቸውን ሲሰዉ በርካታ ቅርሶች በእግሊዝ ተዘርፈዋል፡፡ ከተዘረፉት መካከል ደግሞ እርሳቸው የማርቁት እና ከአጸዱ የሚጠለሉበት ታቦተ መድኃኔዓለም ይገኝበታል፡፡

ፍሊፕ ማርስዲን የጻፉት እና ብሩክ መኮንን በተረጎሙት የቴዎድሮስ እዳ አንዲት ኢትዮጵያ መጽሐፍ ስለ መቅደላ ዝርፊያ እንዲህ ተጽፈዋል፡፡ “ የእንግሊዝ ወታደሮች አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መንግሥታቸው በብዙ ድካምና ልፋት ከየገዳማቱና ከአብያተ ክርስቲያናቱ ያሰባሰቧቸውን ጥንታዊ የብራና መፃሕፍት፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶችን፣ አያሌ መንፈሳዊ ስዕሎችን፣ መንግሥታዊ ሰነዶችን፣ ክብረ ነገሥት የተባለውን ታላቁን መጽሐፍ፣ ዘውዶች፣ ማኅተሞችን፣ ታቦቶችን፣ ከተለያዩ መንግሥታት የተላከላቸውን ያልተገለገሉባቸውን የወርቅና የብር መርገፍ ያላቸው ዣንጥላዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ ዕድሜያቸው ከሺህ ዓመት በላይ የሆኑ የወርቅና የብር መስቀሎች፣ የወርቅ ዋንጫዎች፣ የአቡነ ሰላማ አክሊል ዘውድ፣ ጫማ፣ ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠለቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰለሞን ኒሻን፣ የማዕረግ ልብሶችን፣ የነገሥታቱን የክብር አልባሳትና ጉራዴያቸውን ከየተቀመጡባቸው በማውጣት ተቀራመቷቸው” ተብሏል፡፡

የእግሊዝ ወታደሮች ከዘረፏቸው አያሌ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ባሻገር አያሌዎቹን አውድመዋቸዋል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠፉ ዘንድም ብዙ ጥረዋል፡፡ “ የእንግሊዝ ወታደሮች በመቅደላ አምባ ገብተው በየቤቱ፣ በየጎጆው ከተከማቹት፣ ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ያወደሟቸው፣ የጣሏቸው፣ የሰባበሯቸው በቁጥር ከፍተኛ ብልጫ ነበራቸው፡፡ የብራና መጻሕፍትን ቀዳድደዋል፡፡ አልባሳትንም ሸረካክተዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮሰ በስልጣን ዘመናቸው ያስተላለፏቸውን የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የተጻፉባቸው ሰነዶች፣ የተለያዩ ግዛቶችን ከሚያስተዳድሩ ባለስልጣኖቻቸው ጋር የተለዋወጧቸውን ደብዳቤዎች ከየሳንዱቁ እየተዘረፉ ግማሾቹ በእሳት ሲቃጠሉ፣ ግማሾቹ ከተበተኑበት ሜዳ በነፋስ ኃይል ከአምባው ቁልቁል ሲወርዱ ይታይ ነበር” ተብሎም ተጽፏል፡፡

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረ ሃና ባሕል ጥናት ዳይሬክተር እና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ አፄ ቴዎድሮስ ከታቦተ መድኃኔዓለም ጋር የተለየ ግንኙነት ነበራቸው ይላሉ፡፡ አፄ ቴዎደሮስ ኢትዮጵያን ዳግም አንድ ያደረጉ፣ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት የጣሉ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡

ቴዎድሮስ በገዳማትና በአድባራት ሃይማኖትን፣ ታሪክን፣ እሴትን እና ባሕልን እየተማሩ ማደጋቸው ኢትዮጵያን እንዲረዱ፣ የኢትዮጵያን ኃያልነት እና ታላቅነት እንዲያውቁ አድርጓቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ ሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽዖ በሚገባ አውቀዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቤተክርስቲያኗ ስለ ትናንት ታሪክ፣ ስለ ነገ ተስፋ በሚገባ አስተምራቸዋለች፡፡

የኢትዮጵያን ልክና ታላቅነት በማወቃቸው ሀገራቸውን ወደ ክብሯ እና ወደ ማዕረጓ ለመመለስ ተነሱ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በቤተ ክርስቲያን በማደጋቸው ከታቦተ መድኃኔዓለም ጋር የተለየ ቁርኝት እና ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል ነው የሚሉት፡፡ ከታቦተ መድኃኔዓለም ጋር ለምን የተለየ ግንኙነት ኖራቸው፣ ምክንያታቸው ምን ነበር የሚለው በግልጽ ማወቅ ባይቻልም ታሪካቸው ግን ከታቦተ መድኃኔዓለም ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ይተርካል ነው የሚሉት፡፡

ከደብረ ታቦር ወደ መቅዳላ በተጓዙም ጊዜ ታቦተ መድኃኔዓለምን ወስደዋል፡፡ በደብረ ታቦር እርሳቸው ተቀምጠውበት ከነበረው ስፍራ የመድኃኔዓለምን ቤተክርስቲያን አሠርተው፣ እርሳቸው ከግርጌው ተቀምጠው ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ በደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የክርስትና ስማቸው እየተነሳ ጸሎት የሚደረስላቸው፣ ታሪካቸው የሚዘከርላቸው ንጉሥ መሆናቸውንም ነግረውኛል፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ክብራቸው እና ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ መጠየቅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በቅርቡም ከሀገረ እንግሊዝ የታቦረ መድኃኔዓለም፣ የልዑል ዓለማየሁ የጸጉር ዘለላ እና ሌሎች ቅርሶች ተመልሰዋል፡፡ የተመለሰው የኢትዮጵያ ክብርና ታሪክ ነው ይላሉ የታሪክ መምህሩ፡፡ የተመለሰው የሀገር ክብር ነው፣ የተመለሰው የሃይማኖት ክብር ነው፣ የተመለሰው የኢትዮጵያ ታላቅነት እና ታሪክ ነውም ብለዋል፡፡ ሌሎች ቅርሶች እንዲመለሱ በጋራ መስራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ምሁራን፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅርሶች እንዲመለሱ ግፊት ማድረግ አለባቸውም ይላሉ፡፡

ታሪክን መዘከር እና ጀግናን ማክበር እንደሚያስከብርም ነግረውኛል፡፡ ጀግናን የሚያከብር ጀግና ነው፣ ጀግናን የማይመቀኝ ጀግና ነውም ይላሉ፡፡ ታሪክን ማወቅና ማስታወስ የታሪክ ፍሰቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል፣ በትውልድ ዘንድ መቆርቆር እንዲመጣ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ ታቦታቱ እንደ ቅርስ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቱ በሚያዘው፣ ታሪኩም በሚነግረው መሠረት መቀመጥ አለባቸው ብለዋል፡፡ ታቦታቱ እንዲመሰሉ፣ ተመልሰውም ሕዝብን እንዲባርኩ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ኃያሉ ንጉሥ የሚማጸኑበት፣ የሚመኩበት፣ የሚጸለሉበት፣ ኃይልና ብርታትን፣ ተስፋና ጽናትን ያገኙበት ታቦተ መድኃኔዓለም ለኢትዮጵያውያን መመለሱም ትልቅ ድል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቱርክ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀናቸው።
Next articleለክልሉ ሰላም መረጋገጥ እና ለመልካም አሥተዳደር መስፈን እንደሚሰሩ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የተሃድሶ ሥልጠና ተሳታፊዎች ገለጹ።